መልከ ብዙ ፈተና

መልከ ብዙ ፈተና

በአለምሸት ግርማ

የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እያጠናቀቀ ያለ ወጣት ነው። ቤተሰቡ ሁሉ ተስፋ የጣሉበት። ይሁን እንጂ ትምህርቱን ጨርሶ ችግራችንን ያቃልላል ያሉት ተስፋቸው ተስፋው ጨልሞበታል። በድንገት የጀመረው የኩላሊት በሽታ እሱን ብቻ ሳይሆን መመረቁን በናፍቆት ሲጠባበቁ የነበሩትን ወላጆቹን ሁሉ ተስፋ አስቆርጧል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የመኖር፤ ነገን የማየት ጉጉቱ ተፈጥሯዊ ነውና ለመኖር የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።

እንደዚህ ዓይነት ከባድ የህይወት ፈተና በሚገጥምበት ጊዜ ዙሪያው ጨለማ ሲሆን አማራጭ የተባለው ሁሉ ይሞከራል። በዚህ ምክንያት ነው የዛሬው ወጣት የኩላሊት ህክምና ወጪው ከአቅሙ በላይ በመሆኑ የሰውን ፊት ለማየት የተገደደው። በሚኒባስ ግራና ቀኝ የቀድሞ እና የአሁን ፎቶው ጎን ለጎን በባነር ተሰርቶ ተሰቅሏል። የሰዎችን ትብብር የሚጠይቁት አብረውት ያሉ ወጣቶች ናቸው ታሪኩን በአጭሩ የነገሩኝ።

ሃዋሳ ትልቁ ገበያ መግቢያ ላይ ነው ለዚህ ወጣት የወገን እርዳታ የሚጠየቀው። በልጁ ታሪክ ልቡ የራራ ካለው ላይ ይለግሳል። አንዳንዱም ትቶ ያልፋል። እኔም አቅሜ የፈቀደውን ሰጥቼ አለፍኩ። መኪናው ውስጥ የተባለው ወጣት ጋቢ ለብሶ ተኝቷል። ወጣቶቹ ሰው ባለበት አቅጣጫ ሁሉ እየተዘዋወሩ የሰውን ድጋፍ ያሰባስባሉ።

በእርግጥ ታሪኩ ያሳዝናል። ‘ነግበኔ’ ነውና አብዛኛው የሀገራችን ሰው ለዚህ ዓይነት ችግር ያለውን ያካፍላል። ለተቸገረ ይደርሳል። ለተራበ ያበላል።

ይሁን እንጂ በከተሞች አንዲህ ዓይነቱ ልመና እየተበራከተ ይገኛል። በሰፈር፣ በገበያዎች፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በመናኸሪያ አካባቢ፤ ብቻ ሰው ይበዛበታል ተብሎ በሚታሰብበት አካባቢ ሁሉ እንዲህ አይነቱ ልመና የተለመደ ሆኗል። በእርግጥ ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸው የህመም ዓይነቶች ከታካሚው አቅም በላይ ሲሆኑ በመተጋገዝ አንዱ ሌላውን በመደገፍ ችግራቸው ሲቀረፍ እየተመለከትን እንገኛለን።

በህዝብ ድጋፍ ጤናቸው ተመልሶ ሲያመሰግኑ የታዩም ብዙዎች ናቸው። ለዚህም ማህበራዊ ሚዲያ ትልቁን ሚና እየተወጣ ይገኛል። ማህበራዊ ሚዲያ ከሚያበረክታቸው መልካም አስተዋፅኦዎች መካከል የሰውን ችግር በማጋራት ፈጣን ትብብር እንዲያገኙ ማድረግ ቀዳሚው ነው።

በዚህም ማህበራዊ ሚዲያ ለብዙዎች ህይወት መትረፍ ባለውለታ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በአንፃሩ ታዲያ ይህንን የኢትዮጵያዊነት የመረዳዳት ባህልን ለግል መበልፀጊያነት የሚጠቀሙበትም ከችግረኛ እኩል እየሆኑ ይገኛሉ። በተለያዩ ሚዲያዎች እንደምናየው ሃሰተኛ ቡድን በማደራጀት ለልመና እየተሰማሩ ይገኛሉ።

በቅርቡ ከአዳማ የተነሱ ወጣቶች ዲላ ከተማ አንዱን እንደታማሚ በማስመሰል ሌሎቹ ሲለምኑ በፖሊስ ጥርጣሬ በህግ ቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል። እነዚህ ወጣቶች መኪና ተከራይተው የህክምና ቁሳቁስ አሟልተው ነበር ለዚህ እኩይ ተግባር የተሰማሩት።

ምንአልባት ለዚህ አላማ ያወጡትን ወጪ ለስራ አውለውት ቢሆን እኮ የተሻለ ገቢ ማግኘት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባራት የምር እርዳታ የሚፈልጉትን ውሸታም የሚያስብሉ ናቸው።

በተለይም የእውነት ታመው የወገን ድጋፍ ለሚሹም አስፈላጊው ድጋፍ እንዳይደረግላቸው እንቅፋት ይሆናሉ። እንዲህ ዓይነት ተግባራት እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህላችንን ከማቀጨጩም በላይ የተቸገረን አይቶ እንዳላየ የማለፍ ባህል እንዲዛመት ያደርጋሉ። ሃሰተኞች እየተበራከቱ ሲመጡ እውነተኞችም ደጋፊ ያጣሉ። ስለዚህ ጥቂቶች የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ወይም ያለአግባብ ለመበልጸግ በሚያደርጉት ብልሹ ተግባር ብዙዎች ደጋፊ በማጣት ለስቃይ እንዲሁም ለህልፈተ ህይወት እንዲደረጉ ምክንያት እየሆነ መጥቷል።

ይህ እንዳይሆንና በትክክል የተቸገረ ወገንን መደገፍ ይቻል ዘንድ መንግስት እርዳታ የሚጠይቁ አካላትን በአግባቡ ሊቆጣጠር እና ክትትል ሊያደርግባቸው ይገባል።