“ስራ ያከበሩትን ያከብራል” – ወ/ሮ ፋጡማ ሙባረክ

“ስራ ያከበሩትን ያከብራል” – ወ/ሮ ፋጡማ ሙባረክ

በገነት ደጉ

ወ/ሮ ፋጡማ ሙባረክ የስራ ፍቅር ያላቸው ብርቱ ሴት ናቸው፡፡ ስራን ሳይንቁ መስራት እራስን ያስከብራል ይላሉ፡፡ ሴቶች የሌላ ሰዎችን እርዳታ ሳይሹ እችላለሁ የሚል ወኔ ሊኖራቸው እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

ቀደም ሲል በስልጤ ባህላዊ የኪነት ቡድን ውስጥ ተቀጥረው በውዝዋዜና በድምፃዊነት እየሰሩ እንደነበር ገልፀውልናል፡፡

ወ/ሮ ፋጡማ ሙባረክ የተወለዱት በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ልዩ ስሙ በኬ 01 ቀበሌ በሚባል አካባቢ ነው። ያደጉት ደግሞ አዲስ አበባ መሆኑን ይናገራሉ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ቤተሰቦቻቸው ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲማሩ በመፈለግ ወደ አዲስ አበባ አመሩ፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ሳሪስ ስብስቴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ወላጅ አባታቸው ሴት ልጆቻቸው ተምረው ለቁም ነገር እንዲደርሱ ከነበራቸው ምኞት የተነሳ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ በወላጅ እናታቸው ሞት ምክንያት ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰው ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ወራቤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር መገደዳቸውን ወ/ሮ ፋጡማ አስረድተዋል።

ነገር ግን ከ10ኛ ክፍል በኋላ ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም። የታናናሽ እህቶቻቸው ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ ላይ ወደቀና እነሱን ማሳደግና ማስተማር የዘወትር ተግባራቸው ሆነ፡፡

ወላጅ አባታቸው ትምህርት እንዲማሩ ቢፈልጉም ልጆች እንዳይጎዱ በሚል ትምህርታቸውን ለማቆም ተገደዱ፡፡ በዚህም እህቶቻቸውን በእንጀራ እናት እንዲያድጉ አለመፍቀዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

“በምንም ነገር ተስፋ አልቆርጥም፤ ሰርቼ እንደምለወጥ እምነት አለኝ” ሲሉም ነው የተደመጡት፡፡

በትምህርት ቤት ቆይታቸው በተለያዩ ክበባት ውስጥ ይሳተፉ እንደነበር ይናገራሉ። ይህም ለስኬታቸው እንደጠቀማቸው አስረድተዋል፡፡ በስራ ተንቀሳቅሰው በሚያገኙት ገንዘብ ታናናሽ እህቶቻቸውን ያስተምራሉ፡፡

ትምህርታቸውን ተምረው ትልቅ ደረጃ እንደሚደርሱ ህልም ነበራቸው፡፡ ከእናታቸው ሞት በኋላ ግን ብዙ ታግለው ጥረት ቢያደርጉም ገና የ9ኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ጊዜ ወደ ትዳር ለመግባት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ብዙዎች በሙዚቃው እንዲቀጥሉ ያበረታቱአቸው እንደነበር ወ/ሮ ፋጤ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸውም በወቅቱ ወደ ኪነጥበቡ ለማዘንበል እቅድና ፍላጎቱ እንደነበራቸው ገልፀውልናል። ወደ ጥበብ መጥተው በውዝዋዜም ይሁን በድምፅ ለመስራት እየሞከሩ ብዙም ሳይገፋ ማቋረጣቸውን ያስረዳሉ፡፡

በወቅቱም የሙዚቃ ጥላቻ ኖሮአቸው ሳይሆን ከራሳቸው ቤተሰባዊ ችግር ምክንያት እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡

የአካባቢውም ይሁን የአቻ ግፊት ወደ ትዳር እንዲገቡ ሲያስጨንቋቸው ካለፍላጎታቸው በልጅነት ዕድሜያቸው ወደ ትዳር ዓለም መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡

ከትዳር አጋራቸው ጋር እህቶቻቸውን አብረው እንደሚያሳድጉ ተስማምተው ነበር የገቡት፡፡ ያም ሆኖ በትዳራቸው እምብዛም ሳይገፉ ትዳራቸው መበተኑን ይናገራሉ፡፡

ሁለት ልጆችን ካፈሩ በኋላ ከትዳር አጋራቸው መለያየታቸውን ያስታውሱታል።

ባለቤታቸው ትቶአቸው ወደ አረብ ሀገር እንደሄደም አስረድተዋል፡፡ “መጎዳት ያጠነክራል” ያሉት ወ/ሮ ፋጡማ ተስፋ ሳይቆርጡ ለአንድ ዓመት ያህል ልጆቻቸውን ይዘው ከባለቤታቸው ቤተሰብ ጋር መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ግን አልዘለቁም፡፡ ዳግመኛ ጥለውት ወደ መጡበት ቲያትር ተመለሱ። ለዚህ ደግሞ ጓደኞቻቸው ያደረጉላቸው ድጋፍ የተለየ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በወር 900 ብር እየተከፈላቸው ከልጆቻቸው ጋር መኖር ጀመሩ፡፡ ከስራው የሚያገኙት ደመወዝ በቂ ስላልነበረ ጎን ለጎን ሻይ ቡና መስራት መጀመራቸውን ያስታውሳሉ፡፡

የልጆች እናት ስለነበሩ በቲያትሩ ብዙም ገፍተው ሳይሄዱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከቲያትር ጥበብ መሰናበታቸውን ያስረዳሉ። የቡናውን ስራ ግን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡

የሻይ ቡና ስራው እያደገ በእህታቸው ድጋፍ ሌላ ቦታ ላይ ቁጥር- 2 ብለው መክፈታቸውን ይናገራሉ፡፡ ሳይቆዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁጥር-3 መክፈታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስራን ይንቃሉ። በተለይም ከቡና ትርፍ የሚገኝ አይመስላቸውም፡፡ ነገር ግን የሚያውቋቸው ሰዎች ስለሚያበረታቱአቸው ገበያው ጥሩ እና አዋጭ ነበር ብለዋል፡፡ በቀጣይ በፈጣሪ ፈቃድ የተሻለ ነገር ለመስራት ህልም አለኝ ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ወ/ሮ ፋጡማ ስራ ሙሉ ሰው እንደሚያደርግ እምነት አላቸው፡፡ የሰው እጅ ከማየት እርሳቸውንና ልጆቻቸውን ዛሬን እንዲያዩ ያደረጋቸው በርትተው መስራታቸው እንደሆነ ያምናሉ፡፡

”በሻይና ቡና ስራ ኪሳራ የለም” ይላሉ ወ/ሮ ፋጤ፡፡ በተቻለ አቅም ሙያችንን ተጠቅመን በንጽህና ከቀረበ ሰው ወዶት ይጠቀማል፡፡ ስራ ያከበሩትን ያከብራል” ይላሉ፡፡

ወ/ሮ ፋጤ በስራቸው ውጤታማ ሆነዋል። ከራሳቸው በተጨማሪ ለ7 ሰራተኞች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ልጆቻቸውን በጥሩ ትምህርት ቤት በክፍያ እያስተማሩ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

“ልጆቼን ብቻዬን በጥሩ ሁኔታ ማስተማር መቻሌ ለእኔ ትልቅ ዕድል ነው ብዬ አስባለሁ።” ሲሉም ልጆቻቸውን ማስተማራቸው የፈጠረባቸውን ስሜት ይገልፃሉ፡፡

በሶስቱም ቅርንጫፍ የሚሰሩ ሰራተኞች በወር ከ1ሺ 5መቶ እስከ 2ሺ ብር ተከፋይ ናቸው፡፡ ልጆቻቸው የሚኖሩት አብረዋቸው ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወ/ሮ ፋጤ ወደፊት በዚህ ስራ እንደማይገቱም ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይም እርሳቸውን የተሻለ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችል ስራ ይዘው ብቅ ለማለት ዕቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። ከቡና ሳይወጡ ለደንበኞቻው ትልቅ ባህላዊ ሆቴል የመክፈት ፍላጐት እንዳላቸውም አጫውተውናል፡፡

ባህላዊ ነገር ይዘቱን እና መሰረቱን ሳይለቅ መስራት እንደሚያስቡ ይናገራሉ። እስካሁን በነበራቸው የመኖሪያም ሆነ የስራ ቦታቸው የኪራይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“ለሴቶች መልዕክት አለኝ” ያሉት ወ/ሮ ፋጤ፣ “ከሰራችሁ የማይሳካ ነገር የለምና ኑ አብረን ጠንክረን እንስራ፡፡ የሰውን እጅ አትመልከቱ፡፡ በተለይም በዚህ ኑሮ ውድነት የሰውን እጅ ማየት እጅግ ከባድ ነው” የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡