የኑሮ ውድነቱ አሁንም መፍተሄ ይሻል
በምንተስኖት ካሳሁን
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሸቀጦች ዋጋ በተለይ ደግሞ የምግብ ዋጋ ንረት በብዙ እጥፍ መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ ባዘጋጀዉ አንድ ዓውደ ጥናት ላይ ይፋ በሆነው መረጃ መሠረት የምግብ ዋጋ ንረት ትኩረት ተሰጥቶት ፈጣን የመፍትሄ እርምጃ ካልተወሰደ ከባድ ሃገራዊ ሥጋት ሆኖ እንደሚቀጥል አመላክቷል፡፡
ተቋሙ በትርፍ አምራች እና የምግብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች አካሄድኩት ያለውን የዳሰሳ ጥናት መነሻ አድርጎ ይፋ ባደረገው መረጃ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል። የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም፣ የማምረቻ ወጪዎች መናር፣ የመንግሥት ወጪዎች እንዲሁም የገንዘብ ፍሰት ከትክክለኛው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር አለመጣጣም እና የግብይት ሥርዓቱ አለመዘመን የችግሩ ምንጮች ናቸው ሲል ጠቅሷል፡፡
በጥናቱ ችግሩን ለመፍታት በአጭር ጊዜ ከውጭ ገበያዎች መሠረታዊ የምግብ ምርቶችን ማስገባት እና አቅርቦትን ማሳደግ፣ የገንዘብ ሥርጭትን ከትክክለኛው የኢኮኖሚ እድገት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ በመፍትሄነት የተቀመጠ ሲሆን፤ በረጅም ጊዜ ደግሞ ምርታማነትን መጨመር፣ የእርሻ ኢንቨስትመንቶችን ማስፋፋት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ የምግብ ዋጋ መናር እና የአቅርቦት ችግር በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ግን ሃገራዊ ሥጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው ሲል አሳስቧል፡፡
ጥናቱን መነሻ አድርገን ለማሳያነት የምግብ ዋጋ መናርን ጠቀስን እንጂ የሌሎች ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዋጋ ጣራ መንካቱን በዕለት- ተዕለት ኑሯችን የምንጋፈጠው እውነት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
ለአብነትም የቤት ኪራይ ከነበረበት ቢያንስ በእጥፍ ጨምሯል፤ የመድኃኒት እና የሕክምና አገልግሎት ዋጋ በብዙ እጥፍ ንሯል። በአምስት ብር እንገዛው የነበረ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት በአማካይ በአምስት እጥፍ አድጎ ከ30 ብር በላይ መግዛት ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ የሌሎች መድኃኒቶች ዋጋም በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመሩን ከሰሞኑ ወደህክምና ተቋማት ያቀና ሰው ያውቀዋል፡፡
የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የመጓጓዣ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የአልባሳት እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ዋጋ ጭማሪም በቀላሉ የሚቀመሱ አለመሆናቸውን ለማወቅ የዘርፉ ባለሙያ መሆን አይጠይቅም፡፡
ችግሩ አሁንም የብዙዎች ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ከሚያመላክቱ ምክንያቶች መካከል አንዱን ልጥቀስ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ሂደት ተጎጂ የነበሩት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ብቻ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችም መፈተን መጀመራቸውን ልብ ላለ ጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ያመለክታል፡፡
በአንፃሩ ግን ችግሩን ለመፍታት በሚመለከታቸው አካላት እየተሰራ ነው ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ መረጃዎች በየዕለቱ መስማት ከጀመርን ቢሰነባብትም፤ እየተሠራ ያለው ሥራ ከችግሩ ስፋት እና ውስብስብነት አንፃር በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። ለዚህም ሕዝቡ በተጨባጭ እየተፈተነበት ያለው ኑሮ በቂ ምስክር ነው እላለሁ፡፡
መንግስት ለችግሩ እልባት ለመሥጠት እየሰራ ነው የሚለውን በግርድፉ ጠቃቀስኩ እንጂ ያደጉ ሃገራት በመሰል ወቅት የሃገራቸውን ፖሊሲ በማሻሻል የሥራ ባህላቸውን ቆም ብለው የሚፈትሹበት ጭምር ነው፡፡ እኛም በዚህ ወቅት ምን መደረግ አለበት በሚል የሃገራችንን ፖሊሲ እና የሥራ ባህላችንን መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች መጠናት አለባቸው የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት የሰው ኃይል እና ለም መሬት ይዘን፣ ለልማት መዋል የሚችልና ለሌሎች የሚተርፍ የውሃ ሀብት እያለን፣ በእንስሳት ሀብትም ከአፍሪካ ቀዳሚ ነን እያልን፣ ከፍተኛ የከርሰ ምድር እና ገፀ ምድር ማዕድናት ባለቤት ሆነን ከችግር መውጣት ለምን አቃተን? የማይነጥፍ የሃብት ምንጭ ላይ ተኝተንስ በተደጋጋሚ የሚጎበኘንን ርሃብ መግታት ስለምን አልቻልንም? የሚሉትን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ምሁራን ችግር ፈቺ ጥናት ማካሄድ አለባቸው እላለሁ፡፡
እነዚህ የዘላቂ መፍትሄ አማራጮች በጥናት እስኪለዩ ደግሞ የአጭር እና የመካከለኛ ጊዜ የገበያ የማረጋጋት እና የነፍስ አድን ሥራዎችን በመከወን የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መሰራት እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህን የማለቴ ምክንያቱ የኑሮ ውድነቱ ከድርቅ እና ርሃብ ጋር ተዳምሮ በየአካባቢው “ከመሞት መሰንበት” በሚመስል ሁኔታ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እጆቻቸውን ለምፅዋት ሲዘረጉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡
በመሆኑም እንደ ሃገር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እንደ “ሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ አሻራ” መርሃ-ግብር ያሉ አሳታፊ ሥራዎችን በማጠናከር ዘርፉ እንዲሻሻል መሥራት ከወትሮ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ግን ምርታማነት ይበልጥ እንዲጨምር እድል የሚሰጠውን ዜጎች ይበልጥ ውጤታማ እሆንበታለሁ ወደሚሉት አካባቢ በነፃነት ተዘዋውረው እንዲያመርቱ እና ለገበያ እንዲያቀርቡ በነፃነት ተዘዋውሮ የመሥራት መብት በተሟላ መንገድ እንዲረጋገጥ መሥራት ከመንግስት ይጠበቃል።
ይህን ማድረግ ሲቻል ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና ዜጎች ሙሉ ጊዜያቸውን በልማት ሥራ ላይ እንዲያውሉ በማድረግ የኑሮ ውድነትን መቀነስ የሚያስችል አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል፡፡
በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚያጋጥመውን የፀጥታ መደፍረስ በዘላቂነት በመፍታት ፆም የሚያድር ማሳ እንዳይኖርና ምርታማነት ይበልጥ እንዲያድግ በማድረግ የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት፣ ምሁራን እና መላው ሕብረተሰብ የበኩሉን ሚና በመወጣት ለችግሩ ዕልባት በጋራ ሊሰሩ ይገባል እላለሁ ቸር ይግጠመን! ሠላም ለኢትዮጵያ!
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ