ለልጁ የመሰለፍ ዕድልን የሰጠው ሌላኛው አሰልጣኝ

ለልጁ የመሰለፍ ዕድልን የሰጠው ሌላኛው አሰልጣኝ

አሰልጣኝ ሮቢን ቫን ፐርሲ ለ19 አመት ልጁ ሻኩዌል በፌይኖርድ ዋናው ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ እድል ሰጥቶታል።

የሮተርዳሙ ክለብ ትናንት ምሽት በዩሮፓ ሊግ በሜዳው በሴልቲክ 3 ለ 1 በተሸነፈበት ጨዋታ አጥቂ ቦታ ላይ የሚጫወተው ሻኩዌል 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በመግባት ለዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን አከናውኗል።

ሁለት ዓመታትን በማንቸስተር ሲቲ አካዳሚ ቆይታ ያደረገው ሻኩዌል በፈረንጆቹ 2017 ነበር አባቱን ተከትሎ ወደ ፌዬኖርድ ያመራው።

በፌይኖርድ የመጀመሪያ የፕሮፌሽናል ኮንትራቱን በ2022 ፈርሟል።

ዋና አሰልጣኙ የ19 ዓመት ልጁን ሻኪል ቫን ፐርሲን ባለፈው ሳምንት በኤርዲቪዜ ጨዋታ ለፌይኖርዱ ዋናው ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጨዋታው ስኳድ ውስጥ አካቶት ነበር።

ትናንት ምሽት ግን ተቀይሮ በመግባት ለዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ማከናወን ችሏል።

ሮቢን ቫንፐርሲ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጠው አስተያየት “ቡድናችን ጎል ያስፈልገው ነበር ቅያሪው የተደረገው እንደ አሰልጣኝ እንጂ እንደ አባት አልነበረም” በማለት ተናግሯል።

የቀድሞ የአርሰናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ዝነኛው አጥቂ ለገዛ ልጁ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ ዕድል የሰጠ ብቸኛው አሰልጣኝ አይደለም።

ከዚህ ቀደም ሌላኛው ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ሁዋን ክራይፍ በባርሴሎና ሳሉ ለአብራካቸው ክፋይ ጆርዲ ክራይፍ ለዋናው ቡድን የመሰለፍ ዕድል መስጠታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም አሰልጣኝ ስቲቭ ብሩስ ለአሌክስ ብሩክስ፣አሰልጣኝ ሀሪ ሬድናፕ ለልጃቸው ጄሚ ሬድናፕ እንዲሁም አሰልጣኝ ዚኔዲን ዚዳን በሪያል ማድሪድ ሳለ ለልጆ ኤንዞ እና ሉካ ዚዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍ ዕድል መስጠቱ አይዘነጋም።

የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዋና አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሚዮኔም  ለልጃቸው ጁሊያኖ ሲሚዬኔ በኮልቾኔሪዎቹ ቤት የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ