የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ከማዳበር ባለፈ ህብረተሰቡ በቆጠበው ልክ ብድር አግኝቶ መልማት እንዲችል ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
አርሶ አደሩ በበጋ ወቅት የደረሰውን የቡና ምርት ሸጦ ከሚያገኘው ገቢ መቆጠብ እንዲችል በአቅራቢያው የሚገኙ የቁጠባ ህብረት ሥራ ተቋማት ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠሩ ተናግረዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ፍቅሩ ጠገኖ፤ የቁጠባና ብድር ማህበራት በወረዳው ከፍተኛ የቡና ግብይት በሚኖርበት ወቅት ማህበረሰቡ ከቡና ሽያጭ የሚያገኘውን ገንዘብ እዲቆጥብ በትኩረት መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል
የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ለአካባቢው ኢኮኖሚ መዳበር እና ብልጽግና የጎላ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በመጠቆም፤ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ሀብት ማሰባሰብ ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ መንገሻ እንዳሉት፤ በ2017 ዓ.ም ከ30 በላይ የገንዘብ እና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት እንደነበሩ አስታውሰው በተደረገው ሪፎርም ወደ ሁለት ማህበራት በመዋሃድ ቢፎሚ እና ደራሮ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት በመሆን ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ብድር በማሰባሰቡ ሥራ ከ1 ሚሊዮን 3 መቶ ሺህ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ጅምሩን በመገምገም በአካባቢው ካለው ሀብት አኳያ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በቡና ወቅት ሀብት እንዳይባክን ማህበራቱ ተጠናክረው በማሰባሰብ ለአካባቢው ልማት እና ብልፅግና የበኩላቸውን እንዲወጡ የድጋፍና ክትትል ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
አቶ ፈይሳ ገመደ እና ገረሙ አለማየሁ የቢፎሚ እና የደራሮ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ሰብሳቢዎች ናቸው። አምና የጀመሩትን ቁጠባና ብድር የማሰባሰብ ተግባር አጠናክረው በማስቀጠል የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል እንዲያድግና ቆጥቦ በመበደር ወደ ልማት እንዲገባ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በይርጋጨፌ ወረዳ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት በአዲስ መልክ ተደራጅተው አርሶ አደሮቹ በሚኖሩበት ቅርብ ቀበሌ እና መንደር ገብተው እንዲቆጥቡ በመሥራታቸው የቁጠባ ባህላቸው እያደገ መምጣቱን አርሶ አደር ዝናቡ ደያሶ እና ፈይሳ ገመዳ ገለልፀዋል።
በተለይም በበጋው ወቅት ያመረቱትን ቡና የሚለቅሙበት እና ገንዘብ የሚያገኙበት ጊዜ በመሆኑ ያገኙት ገንዘብ ያለአግባብ እንዳይባክን የደራሮ እና ቢፎሚ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት በቅርበት በመከታተል እንዲቆጥቡ እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ማህበራቱ፤ ተበድሮ በግል የልማት ተግባራት ላይ ለማዋል ቀድሞ መቆጠብ እንደሚገባቸው በማስረዳት እና ግንዛቤ በማስጨበጣቸው የበለጠ ተነሳሽነትን እንደፈጠረባቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አብዶ አያላ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ከማዳበር ባለፈ ህብረተሰቡ በቆጠበው ልክ ብድር አግኝቶ መልማት እንዲችል ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

More Stories
የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በማልማት ለሀገራዊ እምርታ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ
የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
“ሰርተን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከፍ እናደርጋለን” – አቶ ዮሐንስ መላኩ