የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መንግስት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት አስታወቀ።
በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በወልቂጤ ግብርና ምርምር ማእከል የተሰሩ ስራዎች የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድሪባ ገለቴ፥ ተቋሙ በሰብል ዘርፍ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያመነጭ እንዲሁም በእንሰሳትና በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍም ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያወጣ ተናግረዋል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ መነሻ የሚሆኑ ዘሮችን በማባዛት በስፋት ለሚያባዙ አካላት እንደሚሰጥ የጠቆሙት ዶ/ር ድሪባ፥ እነዚህንና መሰል ስራዎችን በመስራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ኢንስቲቲዩቱ የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
የግብርና ሽግግር ምርምር ላይ እንደሚመሰረት አውስተው፥ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በዋለባቸው በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በድንችና በመሳሰሉ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ምርታማነትን ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።
የአፈር አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎች በመዝራት ኖራ በአርሶ አደር ማሳ እየተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደሃገር የተጀመረውን በምግብ ራስን የመቻል ጉዞን ለማፋጠን በሚደረገው እንቅስቃሴ ስንዴ ከውጭ ማስገባት ማስቀረት መቻሉን ያነሱት ሀላፊው በቀጣይ ይህን ውጤት አልቆ ለማስቀጠል የግብርና ምርምር ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው ዞኑ ከወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመቀናጀት አበረታች ተግባራት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ግብርና ለስራ እድል ፈጠራ፣ የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል፣ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ፣ የገቢ አቅም ለማሳደግና ከውጭ የሚገቡ የግብርና ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በመሬት መሸርሸርና በአፈር አሲዳማነት ምክንያት ከጥቅም ውጭ የነበሩ መሬቶች በተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንዲያገግሙ ማድረግ መቻሉንም ዋና አስተዳዳሪው አክለዋል።
በተለይም የመስክ ምልክታ የተደረገበት አካባቢ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመሰራቱ መሬቱ አገግሞ አርሶ አደሮችን ገብስና ስንዴ በማምረት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
አያይዘውም የጠረጴዛማ እርከን ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችል መኖ በመትከል ከእንስሳት እርባታ ምርታማነት ጋር አስተሳስሮ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማእከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቤተል ነክር እንዳሉት ማእከሉ የተሻሻሉ፣ አዳዲስና ውጤታማ የሆኑ ልዩ ልዩ የገብስ፣ የጤፍና የመኖ ጨምሮ ሌሎችም ዝርያዎችን በስፋት የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ ነው።
ማእከሉ በኦሮሚያና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ ጉብኝት የተደረገበት በጉራጌ ዞን የጉመር ወረዳም የዚሁ አካል መሆኑንና ጉብኝቱም የተሰሩ ስራዎች ለማስፋት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት።
ከዚያ ቀደም አርሶ አደሩ ጋር ከደረሱ የምርምር ውጤቶች በተጨማሪ ሌሎችም ከኋላ ሊከተሉ የሚችሉ አዳዲስ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የምርምር ማእከሉ አሲዳማ አፈር ከተጎዳ ኖራ እንዲሁም የምርታማነት እጥረት በሚኖርበት ሰዓት አዳዲስ ዝርያዎችን በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ እየሰራ ይገኛልም ያሉት አቶ ቤቴል ይህም እንደየአካባቢ ስነምህዳር የሚቀርብ በመሆኑ በየአካባቢው ያለውን የመልማት ፀጋን አጉልቶ ከማውጣት አንፃር ትልቅ እድል ይሰጣልም ብለዋል።
በዘንድሮ አመትም አንድ መቶ 18 የሚሆኑ የተለያዩ የሰብል አይነቶች ምርምሮች እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በ218 ሂክታር ላይ የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
በተለይም በጉራጌ ዞን አሲዳማ አፈርን ተቋቁሞ ምርት መስጠት የሚችሉና ምርታማነታቸው ከፍ ያሉ የሰብል ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ከማስገባት አንፃር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በሽታን የሚቋቋሙ እና ምርታማነታቸውን የተረጋገጡ ዝርያዎች ለአርሶአደሩ በማስተላለፍ ረገድ የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ገልፀዋል።
ማእከሉ አሲዳማነትን በማከም ምንም አይነት ግልጋሎት የማይሰጡ መሬቶችን ምርት እንዲሰጡ በማድረግ እንዲሁም በእንሰሳት ዘርፍም እያደረገ ያለው አበርክቶ አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶአደሮች በሰጡት አስተያየት ማእከሉ ባደረገው ድጋፍና ክትትል ከዚያ ቀደም ፆሙን ያድር የነበረን መሬት ወደ ምርት ሰጪነት መሸጋገር በመቻሉ መደሰታቸውንና ይህም ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
“ሰርተን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከፍ እናደርጋለን” – አቶ ዮሐንስ መላኩ
ለኢኮኖሚ እድገት የሚያግዙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መነቃቃት እያሳዩ መሆናቸው ተገለጸ
የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በእንስሳትና ንብ ማነብ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ