“ሰርተን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከፍ እናደርጋለን” – አቶ ዮሐንስ መላኩ
በምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ በአርሶ አደሮች የመስክ ትምህርት ቤቶች የተሰሩ ስራዎች ላይ ከዳውሮ ዞን አርሶ አደሮች ጋር የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።
በስፍራው ከተከናወነው የመስክ ምልከታ በኋላ ውይይትም ተደርጓል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አማካሪና የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ፤ የግብርና ስራን ማዘመን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትንና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ ዘርፉን የምርምር ማዕከል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚሀም መንግስት ለዘርፉ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅቶ ወደስራ መግባቱን አንስተው፤ ይንን ለማሳካትም ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከደጋፊ አካላት አንዱ የሆነው ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር (PACT) የአርሶ አደሮችን አሰራር ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች በተሟላ፣ በተጓደለ፣ በኮምፖስትና ያለምንም ግብዓት ሰርተው የተሻለውን እንዲመርጡ ለማድረግ (PACT) እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአርሶ አደሮች የመስክ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
“የግብርናውን ዘርፍ በማዘመንና የልምድ ልውውጥን በማጠናከር ሰርተን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከፍ እናደርጋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የዳውሮ ዞን አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ከተመለከቷቸውን የምርምር ስራዎች ልምድ ወስደው እንደሚተገብሩ ገልጸዋል።
መሰል የልምድ ልውውጥ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ ገባርኩ ቀበሌ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ ሰርተው በተመለቱት የምርታማነት መጠን መሠረት የአሰራር ዘዴንና የሰብል ዘሮችን መምረጣቸውን ተናግረዋል።
ተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብረት ሽግግር (PACT) በምዕራብ ኦሞና በዳውሮ ዞኖች፣ በሶስት ወረዳዎች፣ በ5 ሺ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ከ25 ሺ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
ለኢኮኖሚ እድገት የሚያግዙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መነቃቃት እያሳዩ መሆናቸው ተገለጸ
የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በእንስሳትና ንብ ማነብ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ
በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ ተጠቆመ