ለኢኮኖሚ እድገት የሚያግዙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መነቃቃት እያሳዩ መሆናቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መስፋፋትና ለኢኮኖሚ እድገት የሚያግዙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መነቃቃት እያሳዩ መምጣቱን የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ገለጹ።
በዳካ ከተማ አስተዳደር ከ20 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ጌሻ ገነት ቤተ-በደሌ ሆቴል ተመርቋል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መስፋፋት እና የኢኮኖሚ እድገት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማስፋፋት ያለዉ ሚና ከፍተኛ ነዉ ብለዋል።
በዳካ ከተማ የተገነባው የጌሻ ገነት ቤተ-በደሌ ሆቴል በአካባቢዉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጌሻ ወረዳ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኝበት ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ድርጅቱ ይህንን እምቅ አቅምና ዕድሎች ለመጠቀም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ላይ በመሳተፍ ለከተማዉ እድገት የድርሻዉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአካባቢዉ የተፈጥሮ ገጸ-በረከት እና ስነ-ምህዳር ለቱሪዝም ኮንፈረንስ ካለው ምቹነት አንጻር በቀጣይ ሌሎች ባለሀብቶችን ለመቀበልና ተባብሮ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የደካ ከተማ አስተዳደር የለውጡ ትሩፋት ነው ያሉት የከተማው አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ሻጊ ከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አበረታች መነቃቃት እየታየ ነው ብለዋል።
በከተማው ያለውን የሆቴል አገልግሎት ችግር የሚቀንስና ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ገንብቶ ለአገልግሎት ያበቁ ወጣት ባለሀብቶችን አመስግነው በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ከተማ አስተዳደሩ በቂ ዝግጅት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጌሻ ገነት ቤተ-በደሌ ሆቴል በ2016 ዓም ግንባታው በ1700 ካሬ መሬት ላይ ተጀምሮ ለምረቃ መብቃቱን የተናገሩት የሆቴሉ ባለቤት አቶ አሳዬ አለማየሁ ለግንባታው ከ20 ሚልየን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ለወደፊት በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ እቅድ ያለው መሆኑን ገልጸው ሆቴሉ አሁን ላይ ለ56 ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ መሆኑንም አክለዋል።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በእንስሳትና ንብ ማነብ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ
በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ ተጠቆመ
ባለፉት አራት ወራት 5 መቶ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ