ባለፉት አራት ወራት 5 መቶ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ

ባለፉት አራት ወራት 5 መቶ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፣ ህዳር 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ባለፉት አራት ወራት 5መቶ 50 ሚሊዮን 5መቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር  ገቢዎች ጽ/ቤት “ተቋምን በልህቀት ገቢን በስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 በጀት የፋይናንሻል እና የፊዚካል ስራዎች  አፈፃፀም ግምገማና የ2018  በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የምክክር ጉባኤ አካሂዷል ።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር  ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አውላቸው ዮሐንስ እንደገለጹት   የታክስ አስተዳደር ስርዓት ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ፣ በፈቃደኝነት የመክፈል በህልን በማዳበር ፣ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በርካታ  ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

የከተማው ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በከተማው በ2017 በጀት ዓመት 1ቢሊዮን 3መቶ 55ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመው፣ለዚህም ውጤት የአመራሩ፣ባለሙያዎች ፣ባለድርሻ አካላትና ግብር ከፋዮች ሚና የሚደነቅ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ 2 ቢሊዮን 7መቶ 37ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን በዚህም 4ወር ውስጥ 5መቶ 50 ሚሊዮን 5መቶ 44 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን በሪፖርቱ ተገልጿል።

መድረኩ በ2017 ዓ.ም የታዩ ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ልምዶች የተወሰደበትና አቅጣጫ መቀመጡን አቶ አውላቸው ተናግረዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው ገቢ ለከተማ ሁለተናዊ ልማት ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ገቢ ካልተሰበሰበ ትምህርት ፣ጤና አገልግሎት ፣መሰረት ልማቶች ፣ ማሟላት አይቻልም ብለዋል።

የገቢ ጉዳይ ለገቢዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ  አካላት ለገቢ መሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የቅንጅት ችግር ፣በአንዳንድ ባለሙያዎች የሚታየው የስነ-ምግባር ጉድለት፣የደረሰኝ ማጭበርበርና ተገልጋዩ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምድ አነስተኛ መሆንና መስል ጉዳዮች መታረም እንዳለባቸው ከንቲባው አሳስበዋል።

‌‎ ከተሳታፊዎች ለተነሱ  አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽና  ማብራሪያ ተሰጥቷል።

አንዳንድ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎችም ለቀጣይ የ2018 ዓ.ም እቅድን ለማሳካትና የነበሩ ጉድለቶችን ለመቅረፍ ልምድ የተወሰደበት መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።

በ2017 ዓ.ም የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላትና ተቋማት የዕውቅና ሰርትፊኬትና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል።

ዘጋቢ :- ታምራት አለሙ ከሆሳዕና ጣቢያችን