መሰናክሎችን ወደ ዕድል የቀየረች ታታሪ እናት
ወ/ሮ ሃዒሻ አብሽሮ ይባላሉ ነዋሪነታቸው በስልጤ ዞን ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ አዳዘር ሼበል ቀበሌ ነው።
ገና ወደ ግቢያቸው ሲገባ ለአይን የሚማርክ አዕምሮን የሚያሳርፍ ትዕይንት ያለው ሲሆን ውብ ዘመናዊው መኖሪያ ቤታቸው በአንድ በኩል ደጃፉ ደግሞ ዙሪያውን በልዩ ልዩ ማጌጫዎች ተውቦ አቀባበል አደረገልንና በግቢው ለእንግዳ ተውበው ከተሰደሩት መቀመጫዎች ላይ አረፍ አልን።
በወ/ሮ ሃዒሻ አብሽሮ ግቢ ያየናቸው ውብ ቤትና ግቢ በሳቸውና በልጆቻቸው ብርቱ ጥረት እውን እንደሆነ አወጉን።
ባለቤታቸው ከዛሬ ስድስት ዓመታት በፊት ከቤት ወጥቶ እንዳልተመለሰ ለኛ መግለፅ በጀመሩበት ቅፅበት ግን በሃዘን ስሜት ተውጠው ንግግራቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።
እኛም ነገሩ አዲስ ሆነብንና ተረጋግተው ሁኔታውን ያስረዱን ዘንድ ከመጠበቅ ባለፈ አብረናቸው በሀሳብ ነጎድን።
ወ/ሮ ሃዒሻ ከገቡበት ስሜት በመውጣት ወደ ታሪኩ ተመልሰው እንዲህ ያወጉን ጀመር።
የትዳር አጋራቸውና የልጆቻቸውን አባት በወቅቱ ከቤት እንዲወጣ ያደረገው ገፊ ምክንያት ብዙ ነበር አሉና በተለይም በዚያን ጊዜ የነበራቸው ሳር ቤት በእሳት መቃጠሉ፣ የእሳቸው ነብሰ ጡር መሆን እንዲሁም በዚህ ሁሉ ችግር ላይ ባለቤታቸው ወንድማቸውን በሞት ማጣት ነው ሲሉ ያለፈውን ስድስት አመት ከጠፋው የትዳር አጋራቸው እያቆራኙ በስሜት ቆዝመው አረዱን።
በወቅቱ የሚያደርጉት ሁሉ ጠፍቷቸው እንደነበር እና በከፍተኛ ጭንቀት እንደተዋጡ ያነሱልን ወ/ሮ ሃዒሻ አብሽሮ፥ ስድስት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ግን የግድ ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው በማመን ፈጥነው ችግሮችን በመጋፈጥ እዚህ መድረሳቸውን ያወጋሉ።
እኛም ወደ መኖሪያ ቤታቸው ስንዘልቅ ከቶ ገጠር ላይ ሊኖር ይችላል ተብሎ የማይታሰብ የከተማ ዘመናዊ ቤቶች ያሟሉትን የእንግዳ ማረፊያ ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ ዘመናዊ ሻወር እና ማዕድ ቤት ያለው ውብ እና ማራኪ ሆኖ ተቀበለን።
በቤታቸው ውበት ተገርመን ወደ ጓሮ እየተሻገርን ይህንን ያማረ ቤት ለመስራት እሳቸውና ልጆቻቸው ብዙ እንደደከሙበት ያነሱልን ወ/ሮ ሃዒሻ፥ በወቅቱ በቃጠሎ የወደመውን ሳር ቤታቸውን በዚህ ዘመናዊ ቤት ተክተው ሲሰሩ የወረዳው አስተዳደር 30 ቆርቆሮ እንደለገሳቸው እና የአከባቢው ማህበረሰብ ደግሞ በጉልበትም በሞራልም ከጎናቸው እንደነበር አወሱን።
ከዛም የሳቸውና የልጆቻቸው ብርቱ የአይበገሬነት ጥረት ታክሎበት ጓሯቸው ላይ ያለውን ሁሉ ለመዘርዘር ይታክታል።
አትክልት፣ ፍራፍሬው፣ የስራስር ተክሎች፣ ቅመማ ቅመም፣ ከእንስሳቱ ደግሞ ንብና ዶሮ በተለይም የእንሰት ተክላቸው ብዛት ሲታይ የወ/ሮ ሃዒሻን ጥንካሬ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
የአከባቢ ዝርያ ላሞች እበት ብቻ ሆኑብኝ ሲሉ የወተት ምርታቸውን አናሳነት የገለፁበት መንገድ ፈገግ አድርጎን ሳለ ዘመናዊ የወተት ላም ለመግዛት 80 ሺ ብር ቅድመ ክፍያ በመስጠት ተመዝግቢያለሁ አሉን።
ወ/ሮ ሃዒሻ ልጆቼ አባታቸውን ካጡበት ጊዜ ጀምሮ እንደ እናትም አባትም በመሆን በቤት ስራውም ሆነ በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ ለማድረግ ብዙ መድከማቸው እንዳለ ሆኖ ልጆቼ የኔን ምክር በመተግበራቸው ነው እዚህ የምታዩትን ሁሉ ማልማት እና መጠቀም የቻልነው፤ ልጆቼም ጠንካራ ተማሪዎች ናቸው ሲሉ የልጆቻቸውን ጥንካሬ አወጉን።
ከግብርና ስራቸው ጎን ለጎን በአከባቢው የሚስተዋለውን የገበያ ክፍተት በማጥናት ከአዳማ ከተማ ቅቤና አይብ በማምጣት እየሸጡ ጎጆአቸውን ከመደገፍ ባለፈ ለሌሎችም አርዓያ መሆናቸውን ወ/ሮ ሃዒሻ ጨምረው ነግረውናል።
የትዳር አጋራቸው ከጠፋ ቀን ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች እያፈላለጉት ቢሆንም ምንም አይነት መረጃ ማግኘት አለመቻላቸውን የነገሩን ወ/ሮ ሃዒሻ ልጆቻቸው የአባታቸው መጥፋት በብዙ እንደጎዳቸው እና እሳቸውም በተመሳሳይ ትካዜ ውስጥ መሆናቸውን ሁኔታቸው ያሳብቅባቸዋል።
ወ/ሮ ሃዒሻ አብሽሮ የገጠማቸውን መሰናክል በጥንካሬያቸው ወደ ዕድል የቀየሩ፣ድህነትን በስራ ማሸነፍ እንደሚቻል ብሎም በገጠር ዘመናዊ ህይወት መምራትን ለሌሎች ያመላከቱ አርዓያ እናት መሆናቸውን እኛም በስፍራው ተገኝተን በመቃኘት የአይን ምስክሮች ለመሆን ችለናል።።
ዘጋቢ፡ ሃጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ለመጪው ትውልድ የተመቻቸ ሀገር ለመገንባት ግብር ከፋዩ ግብሩን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ
የባስኬቶ ዞን ሽግግር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ እያካሄደ ነው
ችግሮች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃጸም መመዝገቡን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ