ግብር ለአንድ ሀገር ህልውና መረጋገጥ እና ህብረተሰቡ ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ወሳኝ በመሆኑ በአሰባሰብ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

ግብር ለአንድ ሀገር ህልውና መረጋገጥ እና ህብረተሰቡ ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ወሳኝ በመሆኑ በአሰባሰብ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

የሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይትና የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው አለቃ፤ ግብር የዜጎችን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ በመሆኑ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የታክስ ማሻሻያዎችንና የግንዛቤ ስራዎችን በመስራት ሀገር ወዳድ የሆኑ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ማፍራት እንደተቻለ ገልፀዋል።

በግብር አሰባሰብ ወቅት በተሰራው ስራ ውጤት መምጣቱን ያነሱት የጽ/ቤቱ ኃላፊ ፤ ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት 2 መቶ 39 ሚሊዮን 4 መቶ ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 መቶ 51 ሚሊዮን 12 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የአዳዲስ ግብር ከፋዮችን ቁጥር በመጨመርና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር 2 መቶ 76 ሚሊዮን 63 ሺህ 5 መቶ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አቶ ሽፈራው አስገንዝበዋል።

በንቅናቄው መድረክ የተገኙት የሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ደምሴ በበኩላቸው፤ ግብር ለአንድ ሀገር ህልውና መረጋገጥ እና ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ሰፊ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ግብር ለህዝቡ የምንሰጠው ምላሽ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በአሰባሰብ ውቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በማስወገድ ግብርን አሟጦ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት ግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት መውጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግበው ከተሸለሙት መካከል የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ አቶ ተስፋዬ ላቀውና በወረዳው የሊሳና ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብረሃም ላምቤቦ በየበኩላቸው፤ ግብር የዕድገት ሁሉ መሠረት መሆኑን በመገንዘብ ለላቀ ውጤት መብቃታቸውን ገልፀው በቀጣይ ይህንን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ገልፀዋል።

በዕለቱ በቀጣይ ወቅት የተሻለ ግብር መሰብሰብ እንዲቻል ከተለያዩ መዋቅሮች ጋር የግብ ስምምነት የተደረገ ሲሆን ባለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ግምባር ቀደም ግብር ከፋዮች የዕውቅናና የዋንጫ ሽልማት በማበርከት ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን