ለመጪው ትውልድ የተመቻቸ ሀገር ለመገንባት ግብር ከፋዩ ግብሩን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ

ለመጪው ትውልድ የተመቻቸ ሀገር ለመገንባት ግብር ከፋዩ ግብሩን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ

በዳውሮ ዞን የኢሠራ ባሌ ከተማ የ2019 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ለ’ እና ‘ሀ’ የግብር ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ አበራ ግብር ለሀገር ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም የአከባቢው ዕድገትና ልማትን ለማስቀጠል ግብርን በወቅቱ በታማኝነትና በግልጽነት በመክፈል የዜግነት ግዴታችን በአግባቡ መወጣት ስንችል ነው ብለዋል።

አክለውም በገቢ አሰባሰብ ሂደት በማቀላጠፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በጋራ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አቶ አባተ አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ ኡትኖም በሰነዱ መነሻ ሀሳብ የግብር ምንነት፣ የግብር አስላጊነት እና የገቢ ግብር አዋጅ ሕጎች ማሻሻያ ዙሪያ ለንግዱ ማህበረሰብ እና ለባለድርሻ አካላት ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ግብር የአንድ አከባቢ ልማትና እድገት ምሶሶ መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብም ይሁን ባለድርሻ አካላት በመገንዘብ ግብርን በታማኝነትና በፍትሃዊነት ላይ ተመስርተው ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ከንግዱ ማህበረሰብ አቶ አማሮ አስራተ፣ ታይበላ አበራና ሌሎች በሰጡት አስተያየት ታማኝነት ከግለሰብ ይጀምራል፤ ግብር መክፈል ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የእምነት መገለጫም ነው ያሉት

አስተያየት ሰጨዎች በገቢ ግብር ወቅት ለሚቀርበው ቅሬታ የባለድርሻ አካላት በቂና ፈጣን ምላሽን በመስጠት በኩል ትኩረት ተሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።

በንቅናቄ መድረኩም የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣ የነጋዴ ማህበረሰብ ክፍሎችና ሌሎች አካላት በተገኙበት ሀሳብ አስተያየት፣ እንዲሁም ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ አፈወርቅ ኦሹ – ከዋካ ጣቢያችን