በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ ተጠቆመ

በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችል የመስክ ላይ ትምህርትና የአርሶ-አደሮች ልምድ ልውውጥ መርሐ-ግብር በክልሉ ምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ ተደርጓል።

የመስክ ምልከታው “Participatory Agriculrure and Climate Transformation (PACT)” በተሰኘ ፕሮጀክት ድጋፍ የተሰሩ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነው።

በምዕራብ ኦሞ ዞን የማጂ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በድሉ ታደመ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ፤ በመስክ ምልከታው የልምድ ልውውጥ በማድረግና በመማማር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

በክልልና በዞን የበለጠ ውጤታማ መሆን እንዲቻል የታዩ ስራዎችን በሌሎች አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የ“ፓክት PACT)” ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ተስፋዬ ፕሮጀክቱ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል ለሰባት ዓመታት የሚተገበር መሆኑን ጠቁመው÷ በምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ ሶስት ቀበሌያት ላይ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ስርዓተ-ፆታን መሠረት ያደረገ ተሳትፎን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ በሚያደርጉና የህብረት ስራ ማህበራትን በሚያበረታቱ ተግባራት ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት 42 የመስክ ትምህርት ቤቶች መቋቋማቸውን ጠቁመው ፤ የምርት መጨመርና መቀንስ ምክንያቶችን ለመለየት መቻሉን ጠቁመዋል።

በግብርና ስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመቅረፍ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ አርሶ-አደሮቹ እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላል ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ በበኩላቸው ፤ የመስክ ጉብኝቱ በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድና የእውቀት ልውውጥን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ አመላክተዋል።

ግብርና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመው ፤ ለኢንዱስትሪ ሽግግርና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

በተለያዩ ሰርቶ-ማሳያዎች አርሶ-አደሮች ልምድ እንዲለዋወጡ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑንና ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የመስክ ጉብኝት ከማድረግ ባለፈ አርሶ-አደሮች የተመለከቷቸውን ስራዎች ወደየአካባቢያቸው ወስደው ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በመስክ ትምህርት ታግዘው እየሰሩ የሚገኙት አርሶ-አደሮችም በሳይንስ በተደገፈ አሰራር ታግዘው ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን