አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከኋላቀር የአመራረትና አስራረስ ዘይቤ በመላቀቅ አዳዲስ ቴክሎሎጂዎችን ተጠቅሞ ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ገለፁ።

በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ ጎልዲያ ቀበሌ አርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋም በቆላማ አርብቶ አደር ኑሮ ማሻሸያ ወይም/LLRP/ ፕሮጀክት ተግባራዊ የተደረገ በቆሎ፣ ማሽላ እና የተለያየ ዝሪያ ያላቸው የእንስሳት መኖ ልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል፡፡

በማሰልጠኛ ማዕከሉ መልካሳ 2፣ ፓዮነር ሊሙ እና የአካባቢ ዝሪያ በቆሎ በብተናና በመስመር የተዘራ እንዲሁም ማደበሪያ አጠቃቀም ታክሎበት በመሬት ላይ ያለው የምርት አሰጣጡ በተሳታፊዎች መስክ ምልከታ ተደርጓል።

በተመሳሳይ መልካም የተሰኘ የማሽላ ዝሪያ በተለያየ ቀለም ምርት አሰጣጥ የተጎበኘ ሲሆን፥ ሮደስ፣ የሱዳን ማሽላ፣ የእርግብ አተር፣ አልፋ አልፋ እና የላም አተር በእንስሳት መኖ ልማት ከተጎበኙት  መካከል ናቸው።

በበናፀማይ ወረዳ ጎልዲያ ቀበሌ ግብርና ባለሙያ አቶ ደፋሩ ድፋባቸው የቀበሌው ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኤፍረም ሙሉነህ በጋራ እንደገለፁት፥ በቀበሌው አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ተግባር ላይ የተመሠረተ ልምድ እንዲቀስሙ እድል ይሰጣቸዋል።

የደቡብ ክልል አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አይዴ ሎሞዶ በመስክ ምልከታው ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በአርብቶና ከፊል አርሶአደሮች አካባቢ ሁሉ አቀፍ ለውጥ እንዲመዘገብ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የተለያዩ የውሃ አማራጮች በመጠቀም በግብርና ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት፣ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየሠራ መሆኑን አቶ አይዴ አስረድተዋል።

የቆላማ አርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዝቅተኛ የኑሮ ማሻሻያ አስተባባሪ ዶ/ር ኢብራ ገ/መስቀል በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ በዞኑ ስድስት አርብቶ አደር ወረዳዎች የማህብረቡ ኑሮ ሊቀይሩ የሚችሉ በግብርና፣ በእንስሳት ልማትና በሌሎች ሥራዎች ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በጎልዲያ ቀበሌ የተካሄደው የመስክ ምልከታ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ተመሳሳይ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በመስክ ምልከታ የተሳተፉ አካላትም ባዩት ነገር መደሰታቸውን ጠቁመው፥ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራውን ወደመጡበት አካባቢ ለማስፋፋት ልምድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን