የክረምት እግር ኳስ ሻምፒዮናው የተሻለ አቅም ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን የምናፈራበት ነው – የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር
የክረምት ወራት እግር ኳስ ሻምፒዮና በመልካም ስነ-ምግባር የታነፁና የተሻለ ብቃት ያላቸውን ተተኪ ስፖርተኞች የሚፈሩበት መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
በክረምት ወራት የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር አካል የሆነው የእግር ኳስ ሻምፒዮና በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የይርጋጨፌ ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዩኒት አስተባባሪ አቶ በረከት ፉላሳ፤ በተለይም ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይልቅ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ ማሳተፍ የውድድሩ ዓላማ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የእግር ኳስ ሻምፒዮናው የከተማውን የስፖርት ወዳድ ሕዝብ ከማዝናናት ባለፈ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ተተኪ ስፖርተኞችን የምናፈራበትና ለይርጋጨፌ ከነማ እግር ኳስ ቡድን የምንመርጥበት ነው ብለዋል።
በይርጋጨፌ ከተማ ስታዲየም እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ውድድር በከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ስምንት ቀበሌያት ለሻምፒዮናነት እየተፎካከሩ እንዳሉ የጠቆሙት አቶ በረከት፤ ውድድሩም በስፖርታዊ ጨዋነት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት አማኑኤል ኃይሌ፣ መልካምሰው ደጀኔ እና ሌሎችም እንደተናገሩት ሁሉም ቡድኖች አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እንደቀረቡና ውድድሩ የአብሮነት እሴትን ከማጎልበት ባለፈ ጤናማ ሕይወትን ከመገንባት አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
መሰል ውድድሮች ካላቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አኳያ ተገቢውን ትኩረት እና ድጋፍ በመስጠት መሥራት እንደሚገባ ተወዳዳሪ ወጣቶቹ አንስተዋል።
ከሐምሌ 26/2018 ዓ.ም ጀምሮ በይርጋጨፌ ከተማ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የክረምት እግር ኳስ ሻምፒዮናው የፊታችን እሁድ በክብቻ ቀበሌ እና ቡሼ ቀበሌ መካከል በሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ መቋጫውን የሚያገኝ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የክረምት እግር ኳስ ሻምፒዮናው የተሻለ አቅም ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን የምናፈራበት ነው – የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር

More Stories
የፒኤስጂው ኮከብ ኪቪቻ ክቫራትስኬሊያ አዲስ ወኪል መረጠ!
ቼልሲ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ለመሸጥ ቀነ ገደብ አስቀመጠ
“ኤርሊንግ ሀላንድን አምበል የምናደርገዉ ከሆነ ትልቅ ችግር ዉስጥ እንገባለን” ኤንዞ ማሬስካ