ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ የግብርና ልማት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኣሪ ዞን አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ የግብርና ልማት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳሰበ።
የኣሪ ዞን የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ መሐመድ መኮንን እንደገለፁት በአሁን ወቅት ያለው እርጥበታማ የአየር ፀባይ ከክረምት ወደ በጋ መሸጋገሪያ ሲሆን እየጣለ ያለው ዝናብ የማይጠበቅ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
ይህ ወቅቱን ያልጠበቀ የአየር ፀባይ በደረሱ የግብርና ምርቶች ላይ አደጋ የማድረስ አጋጣሚው ሰፊ በመሆኑ አርሶ አደሩ በጥንቃቄ የደረሰ የግብርና ምርቶችን መሰብብብና በአግባቡ ማከማቸት እንዳለባቸው አቶ መሐመድ አሳስበዋል።
በተለይ በአሁን ወቅት የጥራጥሬና የጤፍ የግብርና ምርቶች ለምርት አሰባሰብ ደርሰው በአርሶ አደሩ እየተሰበሰበ ሲሆን በምርቱ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በፍጥነት ከማሳ ላይ ማንሳት ይጠበቃል ሲሉም ሀላፊው አስገንዝበዋል።
በወንዞች ዳርቻ እንስሳት ከማሰር መቆጠብ እንደማያስፈልግና ሰዎችም ወንዞችን ሲሻገሩ በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት መልዕክት ያስተላለፉት አቶ መሐመድ፥ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋና ናዳ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
ጽ/ቤቱ ከብሔራዊ ሚትዮሮሎጂና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚደርሰው መረጃ መሠረት በዞኑ ስር ላሉ መዋቅሮች በየሳምንቱ ረቡዕ ቀን የመረጃ ልውውጥ በማድረግ አደጋ ከመድረሱ በፊት ቅድመ መከላከል ሥራውን በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
የዞኑ ነዋሪዎችም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ገልፀው በዚህም ልዩ ጥንቃቄ እየወሰዱ ስለመሆናቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ
የገጠር ኮሪደር ኤኒሼቲቭ የገጠርሪቱን ኢትዮጵያ አኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የሚያዘምን መሆኑ ተገለጸ
በጥንት አባቶች ተጠብቆ የቆየውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በትኩረት እየተሠራ ነው