የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ

የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በግብርናው ዘርፍ የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ።

በ2018 በጀት ዓመት 140 ቶን የማር ምርት ለማግኘት መታቀዱን የወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስተውቋል።

በወረዳው ሣጌ ቀበሌ በንብ ማነብ ተግባር የተሠማሩ አቶ ደሳለኝ ታደሰ ከ30 በላይ ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎ እንዳለቸው ገልፀው ከዚህም ባለፈው ዓመት ከ150 ኪ.ግ በላይ የማር ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ የገበያ ትስስር ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።

ዘመናዊ የንብ ቀፎ ከወረዳ ግብርና ጽ/ቤት እንደሚያገኙ የተነገሩት አቶ ደሳለኝ ዘርፉ አዋጭ ስለሆነ ማንኛውም ሰው በዘርፉ ቢሠማራ ውጤታማ ይሆናልም ብለዋል።

ሌላው በዚሁ ቀበሌ አሥር ባህላዊ ቀፎ እንዳለቸው የተነገሩት አቶ ወልዴ ዓለሙ ሁሉንም ወደ ዘመናዊ ቀፎ ለመቀየር መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

በሚያገኙት የማር ምርት ኑሮአቸውን እየመሩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ወልዴ በአሁኑ ወቅት በማህበር ተደራጅተው በዘመናዊ ሁኔታ ለማነብ ዝግጅት ማድረገቸውንም ተናግረዋል።

በሀዲያ ዞን የጎምቦራ ወረዳ በማር ምርት ከሚታወቅባቸው አከባቢዎች አንዱ ነው ያሉት ደግሞ በጎምቦራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳት ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ሰላሙ ግርማ ናቸው ።

በወረዳው ከ3 ሺህ 500 በላይ ባህላዊ፣ የሽግግር፣ ባለፍሬምና ዘመናዊ ቀፎዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዶ/ር ሰላሙ ከ1ሺህ በላይ አርሶአደሮች በዘርፉ ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

ዶ/ር ሰላሙ አክለውም በ2017በጀት ዓመት 120ቶን የማር ምርት መገኘቱንና በ2018በጀት ዓመት ደግሞ 140 ቶን የማር ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስረድተዋል ።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ድርጅቶች አማካኝነት ዘመናዊ ቀፎዎች ለተጠቃሚዎች ማቅረቡን ያነሱት አስተባባሪው ህብረተሰቡም በማህበር በማደራጀት ወስዶ እንዲጠቀም አሳስበዋል ።

ዘጋቢ፡ የመንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን