የገጠር ኮሪደር ኤኒሼቲቭ የገጠርሪቱን ኢትዮጵያ አኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የሚያዘምን መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የገጠር ኮሪደር ኤኒሼቲቭ የገጠርሪቱን ኢትዮጵያ አኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የሚያዘምን መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ ገለፁ።
በገጠር ኑሮ ከጨለማና ከጭስ ችግር ተላቀው አዲስ የብርሃን ጸዳል ማየት በመቻላቸው ደስተኞች መሆናቸውን በከምባታ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ የገጠር ኮሪደር ልማት ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአራት ዞኖች ከተሰራው የገጠር ኮሪደር ስራ አንዱ የሆነው የከምባታ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ኮሪደር ተጠናቆ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ( ዶ/ር)ተመርቆ ለነዋሪዎች መበርከቱ የሚታወስ ነው።
በዞኑ አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ሃሚዶ ጎፎሮ ቀበሌ የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑት አቶ በቀለ በካሎ፣ ወ/ሮ አበበች ደግነት እና አቶ ደስታ ቆጬ በገጠር ኮሪደር ከጨለማና ከጭስ ችግር ተላቀን አዲስ የብርሃን ጸዳል ያየንበት ነው ብለዋል።
ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ በመንግስት እንደተሟላላቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የሶላር መብራትና የባዮጋዝ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው በመግለጽ በገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ህወታቸውን በማሻሻል በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በግብርናው ዘርፍ የበለጠ እንደሚሰሩና ልምዱን ለሌሎች በማስፋፋት አከባቢውን ለመለወጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የአዲሎ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ አበበ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 17 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ቀበሌዎች የከምባታ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ሀሚዶ ቀበሌ ለዚህ ሀገራዊ ኢንሼቲቭ መመረጡ ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።
ማሳያ የሆኑ 6 የመኖሪያ ቤቶች በወረዳው ተገንብተው ለነዋሪዎች መሰጠታቸውን በመግለጽ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ይህ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ለኑሮ ምቹ እና ተመራጭ ከመሆኑም በላይ ለሌላው ማህበረሰብ ምርጥ ተሞክሮ የሚሆን እና መነሳሳትን የፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው የገጠር ኮሪደር ኤኒሼቲቭ የገጠርሪቱን ኢትዮጵያ አኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የሚያዘምን ነው ብለዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ከቦታ መረጣ ጀምሮ በርካታ ስራዎች እንደተከናወኑ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የገጠር ኮሪደር ኢንሼቲቭ የኢትዮጵያን ማንሰራራት በገጠሩም የሚያስፋፋ ነው ብለዋል።
የገጠሩን ክፍል መቀየር እንደሚቻል በተጨባጭ ያሳየውን የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
በቅመማ ቅመም፣ በጓሮ አትክልት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በፍራፍሬ ተክሎች የሌማት ትሩፋትን በማስፋፋት አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ አልፎ ለገበያ ማቅረብ የሚችልበትን ምቹ እድል የፈጠረ መሆኑንም አክለዋል።
በቀጣይም በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሰጠውን ተልዕኮ በትጋት ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመው ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ: ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ የግብርና ልማት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በጥንት አባቶች ተጠብቆ የቆየውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በትኩረት እየተሠራ ነው