በስብዕና ግንባታ ስራ ላይ በማተኮር በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ

በስብዕና ግንባታ ስራ ላይ በማተኮር በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ

ጽ/ቤቱ በዲላ ከተማ ለሚገኙ ወጣቶች የስብዕና ልማት ስልጠና ሰጥቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ክንፍ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ዋዳ በስልጠናው ላይ እንደገለፁት፤ ለስኬታማ ሕይወት እንቅፋት የሆኑትን ነገሮች በመለየት ወጣቱ ለተሳካ ህይወት በዕቅድ ሊመራ ይገባል፡፡

ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ እንደሀገር የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የስብዕና ግንባታ ስራ ላይ በማተኮር በስነ-ምግባር የታነፀ ወጣት ለማፍራት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ጽ/ቤቱ በክልሉ ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶችን የስብዕና ልማት ስልጠና ለመስጠት በማቀድ ስልጠናውን በጌዴኦ፣ በወላይታ እና ጋሞ ዞኖች ለሚገኙ ወጣቶች መሰጠቱን አቶ ሚካኤል ጠቅሰው በቀጣይም በቀሩት በክልሉ በሚገኙ ዞኖች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዲላ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መንግሥቱ ተክሌ፤ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እና እድገትን ለማፋጠን በስብዕና የተገነቡ ወጣቶችን ማፍራት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በክረምትም ሆነ በበጋ ወቅት በሚከናወኑ የበጎ አገልግሎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ወጣቱ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፤ ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ወጣቶች በመተግበር በስራ ላይ እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

በስልጠናው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ክንፍ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ዋዳ፣ የክልሉ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አስቻለው መሸሻ፣ የክልሉ ወጣቶች ክንፍ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ወገኔ ወርቅነህ፣ የዲላ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንግሥቱ ተክሌን ጨምሮ የከተማው ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን