ወጣቶች ግጭትን በመከላከል ረገድ ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወጣቶች በሀገር ግንባታ፣ በሰላም ማስፈን እና በማህበረሰብ ውስጥ ግጭትን በመከላከል ረገድ ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ የወጣቶች አስተዋጽኦ በሚል መሪ ቃል ከወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ በቡታጅራ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ፥ ወጣቱ በሀገር ግንባታ ውስጥ ያለው ሚና በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ሊሆን የሚችል ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በድራማ፣ በስነ-ጽሁፍ እና በተመሳሳይ መድረኮች ውስጥ በመሳተፍ ግጭትን ለመከላከል እና የሰላም ባህልን ለማጠናከር ብዙ ዕድሎች እንዳሏቸው ጠቅሰዋል።
ሰላምን ለማስፈን የወጣቱን አቅም በመጠቀም ፋንታ ለክፉ ዓላማ የሚያነሳሱ እና ሀገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ከመከተል መታቀብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
መድረኩ ወጣቶች በሀገር ግንባታ፣ በሰላም ማስፈን እና በማህበረሰብ ውስጥ ግጭትን በመከላከል ሊኖራቸው በሚገባ ሚና ላይ ውይይት እንዲካሄድ ያለመ ሲሆን፥ ለውይይቱ መነሻ የሚሆኑ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ የቀረበው የመጀመሪያ ሰነድ ታሪካዊ ድሎቻችንና ትውፊቶቻችን በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መሆኑን አቶ ተክሌ ሽፈራው በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጠቁመዋል።
ሰነዱ ከታሪካዊ የአድዋና የካራማራ ድሎች ጀምሮ በመጠቀም ትውልዱ ከታሪኩ መማር እንደሚገባው በመጠቆም፥ የዛሬው ትውልድ አዲስ ታሪክ ለመፍጠር መነሳሳት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መሆኑን አቶ ተክሌ ገልጸዋል።
ሌለኛው “ግጭት በመከላከልና ሰላምን በመገንባት የወጣቱ ሚና“ በሚል ርዕስ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ በየነ፥ የውስጥ ግጭቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፥ ወጣቶች ግጭትን ከማባባስ ይልቅ ለግጭቱ የመፍትሔ አካል መሆን እና የሰላም አምባሳደሮች እንዲሆኑ አስገንዝቧል።
ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ ግጭትን የሚያባብሱ እና ደም አፋሳሽ መልዕክቶችን ከማሰራጨት ተቆጥበው አስታራቂ እና ሰላም አስፋፊ መልዕክቶችን እንዲያስተላልፉ በሰነዱ ተመልክቷል።
በሌለ በኩል በስነ-ትውልድ አድን የስነ-ምግባርና ግብረ-ገብነት ግብረ-ሰናይ ድርጅት ባለሙያ አቶ አብርሃም ግምሶ በተቋማት ያለው የስራ ስነ-ምግባር በጥልቀት ተመልክቶ ሁሉም ሰው ራሱን በመገምገም ስነ-ምግባሩን እንዲያሻሽል መልዕክት ተላልፏል።
በተጨማሪ መልካም ስነ-ምግባር ከልጅ አስተዳደግ ጀምሮ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ እና ለሀገር የሚያበረክተውን ትልቅ ፋይዳ በስፋት ተብራርቷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፍ አቶ ተመስገን ካሳ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳ በበኩላቸው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ መንገድ መዝጋት እና መሳል ድርጊቶች ኋላ ቀርነት ግዜን የማይመጥኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ታምሬ አበበ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የጤና ፕሮግራምና ኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ የተግባር አፈፃፀም ግምገማና የውይይት መድረክ ተካሄደ
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በመመዝገብ የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ጥሪ አቀረበ
የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ የትላንት ጉድለቶችን በማከም ዛሬን በሚገባ ተጠቅሞ ነገን በመተለም የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማድረስ መሆኑን የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ