የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከተለመደው አስተራረስ ዘዴ በመላቀቅ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ
ይህ የተገለፀው “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” የሚል ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ያለውን ለውጥ በተመለከተ በ2017 አፈፃፀምና የ2018 ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነው።
መድረኩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ለጋራ ችግሮች በጋራ መፍትሔ መፈለግ ላይ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍለ ጅግሶ እንደገለጹት፣ የግብርና ባለድርሻ አካላት ከአርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት የግብርና ምርትን በማሳደግ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን የግብርና ምርት ውድነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ ይገባል።
በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረተሰቡ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሣደግ የህልውና ጉዳይ ማድረግ እንዳለባቸው ኃላፊው አሳስበዋል።
በመድረኩ የውይይት ሰነዱን ያቀረቡት በወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የምግብ ዋስትና ዳሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን ታደሰ፣ አርሶአደሮች በራሳቸው አምርተው የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
1 ሺህ 2 መቶ 42 የሚሆኑ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ ለታቀፉ አርሶና አርብቶ አደሮች የወተት ላሞች ድጋፍ መደረጉንም ቡድን መሪው ጠቁመው በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የአርሶአደሩን ህይወት ለመቀየር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ፣ የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ ከተረጅነት አስተሳሰብና ተግባር በመውጣት በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከተለመደው አስተራረስ ዘዴ በመላቀቅ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
በተለይ በሰብል፣ በቡና፣ በእንሰት፣ በፍራፍሬ ምርት ላይ በሚገባ ከተሰራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመው ለዚህ ውጤታማነት የአረንጓዴ ልማት ሥራ፣ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ የማሳደግና የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት አስተዳዳሪው አመላክተዋል።
በወረዳው በአጭር ዓመታት በተሠሩ የግብርና ሥራዎች አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ ከመምጣታቸውም በላይ በዘርፉ በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች መፈጠራቸውንና ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውን በማስፋትና የአርሶ አደሮችን ቁጥር ከፍ ማድረግ አለብን ያሉት አቶ ዳዊት፤ ለሀገር ብሎም ለአካባቢ ዕድገት መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በተጨማሪ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ከየቀበሌው የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በ2017/18 የመኸር አዝመራ ምርት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ከ1 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ በፀደይ አዝመራ ለመሸፈን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን በስልጤ ዞን የሁልባራግ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
በስብዕና ግንባታ ስራ ላይ በማተኮር በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአረጋዉያን ያስገነባዉን የመኖሪያ እና እንክብካቤ ማዕከል ስራ አስጀመረ