የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ

የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው ከወልቂጤ ክላስተር የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ጋር በመተባበር “የትምህርት ስብራትን ለመጠገን አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል መርህ በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ በቀቤና ልዩ ወረዳ እና በአበሽጌ ወረዳ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሃይሉ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ መንግስት ማህበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። እየተከናወኑት ከሚገኙ ተግባራት መካከልም የአቅመ ደካማዎችንና አረጋዊያን ቤተሰቦችን መደገፍ አንዱ መሆኑን በማመላከት ይህም በመተባበር መስራት እንደሚቻል ዕድልን እንደሚፈጥር ነው።

በዚህ መነሻነትም ቢሮው በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ በቀቤና ልዩ ወረዳ እና በአበሽጌ ወረዳ ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን በመጥቀስ ተግባሩ ስኬታማ እንዲሆን ላስተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን ቸረዋል።

ሀገርን ለመለወጥ የትምህርት ዘርፍን ቅድሚያ ሰጥቶ መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት።

የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደረገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለፅ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች በርትተው ትምህርታቸውን በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረጉም በተጓዳኝ ወላጆችንም እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት።

ስለሆነም ቢሮው መሰል ድጋፎች አቅም በፈቀደ መጠን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው ለዘርፉ ውጤታማነትም ሁሉም ማገዝ እንዳለበት አቶ ዳዊት ሀይሉ አሳስበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትልና የውሃ አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር በበኩላቸው፤ በክላስተሩ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው ለተማሪዎች የተደረገው ድጋፍም ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መከታተል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የወልቂጤ ክላስተር የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ የፖለቲካ አደረጃጀት ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ገነት ታደሰ፤ ድጋፉ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረው ክንፉ መሰል ድጋፎች በባለፈው ዓመትም ሲያደርግ መቆየቱንና በተለይም በትምህርት ላይ የሚሰራ ስራ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

በቀጣይም መሰል ድጋፎች በሌሎች ዘርፎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማስገንዘብ ለተማሪዎቹ በቀጣይ የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የተማሪ ወላጆች በሰጡት አስተያየት ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በመደረጉ መደሰታቸውን በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችም ከዚህ ቀደም በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ምክንያት ችግር ይገጥማቸው እንደነበር አውስተው ዛሬ የደብተር፣ እስክርቢቶና ቦርሳ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ በትምህርታቸው ጠንክው በመስራት ለተሻለ ውጤት እንደሚተጉ ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የወልቂጤ ክላስተር የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አመራር አባላት፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ ከቀቤና ልዩ ወረዳ እና ከአበሽጌ ወረዳ የተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም ድጋፍ የተደረገላቸው ወላጆችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን