በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ዘርፎች በ70 ሚሊየን ብር ወጪ የተሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች በ70 ሚሊየን ብር ወጪ ሲሰሩ የነበሩት የልማት ፕሮጀክቶች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡
የከተማውን መሠረተ ልማት ለማስፋፋት ገጽታውን ለመቀየር በሚደረገው ልማታዊ ሥራዎች ላይ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በምረቃው መርሃ ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ከተማዋን የሚመጥን የመሠረተ ልማት አውታሮችን በመዘርጋት ለነዋሪዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ ስራዎችን በሚገባ ለማከናወን እንዲሁም የመሠረተ ልማት ስራዎችን በማፋጠን ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል የተባሉ የማሽነሪዎች ግዢ መፈፀማቸውን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ከተማው ለነዋሪው ምቹ፣ ሳቢና ጽዱ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር የከተማ መሪ ፕላን የተከተሉ የከተማ ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ታደለ ጥላሁን፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች በ70 ሚሊየን ብር ወጪ መገንባቱን ገልጸዋል።
ከከተማው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመሠረተ ልማት ስራዎች ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ ታደለ፤ የህዝብን የመልማት ጥያቄ በመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እየተሠሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ዞኑ አሁን ካለበት ወደላቀ ብልጽግና ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በዚህም ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ እንደተናገሩት፤ የከተማውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ተረድቶና በሚገባ ለመጠቀም በመስራት የማህበረሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡
እንደ ከተማው ቀደም ሲል የነበረውን መሠረታዊ የልማት ሥራዎችን በመቅረፍ ሁለንተናዊ ለውጥ በከተማ ልማት ስራዎች ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ዶክተር አበባየሁ አድንቀዋል።
የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከተሞችን ወደላቀ ብልጽግና ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት በውስን አካላት ብቻ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ ማሳካት እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
ከተማው ፈጣን የከተማ እድገት በማሳየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነበረበት ፈርጅ ሁለት ወደ ፈርጅ አንድ ደረጃ ማደጉን ተከትሎ መደሰታቸውን ገልፀው፤ ሁሉ አቀፍ የልማት ተሳትፎ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የማዘጋጀት ቤታዊ አገልግሎት ማዕከል እድሳት፣ የመንገድ መሠረተ ልማት አውታሮች፣ የከተማውን የኮሪደር ልማት ሥራ፣ ፈጣን አገልግሎት መሰጠት የሚያስችሉ የመረጃ ልውውጥ ማዕከላት ይገኙበታል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በክረምት የተከናወኑ የወጣቶች በጎ ተግባራት ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት ሊወጣ የነበረ ወጪ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
የአርሶ አደሩን ገቢና የኑሮ ደረጃ በመሠረታዊነት ለማሻሻል በመንግሥት የተጀመሩ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮችን ማጠናከርና በግብርና ልማት ዘርፍ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
ለይርጋጨፌ ከተማ የፈርጅ 1 እውቅና ተሰጠ