ምግብና ሥርዓተ-ምግብን በማሻሻል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ ገለጸ

ምግብና ሥርዓተ-ምግብን በማሻሻል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ ገለጸ

በቢሮው የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ከምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለእንስሳት እርባታ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው መድረክ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ፤ ባለፉት አራት አመታት በሌማት ትሩፋት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የተሻለ መነቃቃት የታየባቸው ናቸው ብለዋል።

ቢሮው ምግብና ሥርዓተ-ምግብን በማሻሻል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት ሥራን ከተለመደው የእርባታ ዜደ የተሻለ በማድረግ በምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የእንስሳት ተዋጽኦ በኢትዮጵያዊያን ማዕድ ላይ የቅንጦት ምግብ መሆን የለበትም ያሉት አቶ ታመነ፤ ያሉንን ሀብቶች ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክሮ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።

በክልሉ በእንስሳት እርባታው ዘርፍ ከ15 እስከ 20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመው፤ በቀጣይ በስፋት መስራትና የማሳደግ ተግባር የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ ይሆናል ብለዋል።

በሌማት ትሩፋት ፓኬጅ ላይ የተዘጋጀውን የስልጠና ሰነድ በቢሮው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰለች ታደመ እያቀረቡ ይገኛል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን