ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትናንት ምሽት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ከሀንጋሪ ብሔራዊ ቡድን ጋር 2 አቻ በተለያየበት ጨዋታ ተጨማሪ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል።
የ5 ጊዜ የባሎንዲኦር ተሸላሚው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በምሽቱ ጨዋታ ምንም እንኳን ፖርቹጋል በጨዋታው ነጥብ ብትጥልም የተገኙትን ሁለቱንም ጎሎች ሮናልዶ ከመረብ ማሳረፉ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎም የ40 ዓመቱ ተጫዋች ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የምንጊዜም ከፍተኛው ጎል አስቆጣሪ ተጫዋች ሆኗል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ባደረገቻቸው 50 ጨዋታዎች ተሰልፎ በመጫወት 41 ጎሎችን አስቆጥሮ ነው የክብረወሰኑ ባለቤት መሆን የቻለው።
ከአሁን ቀደም የክብረወሰኑ ባለቤት ጓቲማላዊው ካርሎስ ሩይዝ ሲሆን 39 ጎሎችን ነበር ያስቆጠረው።
የ8 ጊዜ የባሎንዲኦር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ በዚሁ የውድድር መድረክ 36 ጎሎችን ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በማስገኘት 3ኛው ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ይገኛል።
የመጀመሪያው እግር ኳሰኛ ቢሊዬነሩ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለስልሳዎቹ በሁሉም ውድድሮች 225 ጨዋታዎችን አከናውኖ 143 ጎሎችን በማስቆጠር በአጠቃላይ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆኑም እንዲሁ ይታወቃል።
በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ 948 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻለው ኮከቡ ተጫዋች የጎል መጠኑን 1 ሺህ ለማድረስ በመገስገስ ላይ ይገኛል።
የማዴራው ፈርጥ እዚሁ ቁጥር ላይ ለመድረስ የቀሩት 52 ጎሎች ብቻ ናቸው።
እድሜ በጨመረ ቁጥር እንደወይን እየጣፈጠ የሚገኘው የትጋት ተምሳሌቱ ተጫዋች እስካሁን በክለብ ደረጃ ለ5 የተለያዩ ክለቦች መጫወት ችሏል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ እግር ኳስ መጫወትን በጀመረበት ስፖርቲንግ ሊዝበን 5 ጎሎችን ሲያስቆጥር ሁለት ጊዜ መጫወት በቻለበት ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ 145 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።
በወቅቱ የዓለማችን ውዱ ፈራሚ አድርጎት ላስፈረመው እና በርካታ ስኬቶችን እንዲያጣጥም ላስቻለው ሪያል ማድሪድ 450 ግቦችን በማስቆጠር የሎስብላንኮዎቹ የምንጊዜም ከፍተኛው ጎል አስቆጣሪ ተጫዋች ነው።
ለጁቨንቱስ 101 ጎሎችን ሲያስቆጥር ረብጣ ዶላሮች እየተከፈሉት አሁን ላይ እየተጫወተ ለሚገኘው አልናስር እንዲሁ እስካሁን 104 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
አትሌት መሠረት ደፋር የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ሽልማት ተበረከተላት
ማርቲን ኦዴጋርድ ለአንድ ወር ያህል ከሜዳ ይርቃል
ሞሮኮ አሜሪካን በማሸነፍ ለግማሽ ፍፃሜ ደረሰች