አትሌት መሠረት ደፋር የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ሽልማት ተበረከተላት
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ላይ የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ በአትሌቲክሱ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሽልማት ተበርክቶላታል።
ከአትሌት መሠረት በተጨማሪ በየአመቱ ስኬትንና የላቀ ስራ የሰሩ ልዩ ተሸላሚዎች ከኪነጥበብ፣ ከቢዝነስ ዘርፍ ተመርጠው ላደረጉት በጎ አስተዋፅኦ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዘንድሮ የሽልማት መርሀግብሩ ላይ በአትሌቲክሱ የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ አትሌት መሠረት ደፋር በዓለም መድረክ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጓን ተከትሎ ነው የተበረከተላት።
አፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ እስካሁን ለአራት ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን በ2019 ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ በ2021 አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ በ2022 አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ በ2023 የዲባባ ቤተሰብና አትሌት ስለሺ ስህን እና በ2024 አትሌት ትዕግስት አሰፋና ጉዳፍ ፀጋይ ተሸላሚ የሆኑ የኢትዮጵያ ጀግና ልጆች ናቸው።
የኦሎምፒክ እና የአለም ሻምፒዮኗ አትሌት መሠረት ደፋር በዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ኮከብ አትሌት ምርጫን በሴቶች ዘርፍ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት መሆኗ ይታወቃል፡፡
በሽልማት መርሀግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የአሜሪካ ሴናተሮች፣ ከንቲባዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸዉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያስረዳል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ማርቲን ኦዴጋርድ ለአንድ ወር ያህል ከሜዳ ይርቃል
ሞሮኮ አሜሪካን በማሸነፍ ለግማሽ ፍፃሜ ደረሰች
ኤርሊንግ ሀላንድ 50 ጎሎች ላይ ፈጥኖ የደረሰ ተጫዋች ሆነ