በተጀመረው የፍራፍሬ ልማት ሥራ ተጠቃሚ ሆነናል- አርብቶ አደሮች
ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርብቶ አደር አካባቢ በተጀመሩ የፍራፍሬ ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን በደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለፁ።
አርብቶ አደሮቹ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ የሙዝና ፓፓያ ዝሪያዎችን በስፋት እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።
በማህበር በመደራጀት ባከናወኑት የፍራፍሬ ልማት ሥራ ከሙዝና ከፓፓያ ከ2 መቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተናል ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነቱን የልማት ሥራ በአካባቢያቸው እንደማያዉቁ የሚገሩት አርብቶ አደሮቹ ቀደም ብለው የፍራፍሬ ልማት ሥራውን ጀምረውት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ኢኮኖሚያቸው በብዙ እጥፍ ያድግ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የኛንጋቶም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ሎኮርማ ጅምር ስራዎችን በሁሉም ቀበሌ በማስፋፋት ወረዳው በሁሉም የግብርና ምርቶች እንዲተዋወቅ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
የዞኑ ምክር ቤቶች ምክክር መድረክ በወረዳ የተደረገ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎች አጠቃላይ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የተገኘውን ስኬት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ የገለፁት የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ በተለይ ወጣቶች በኢኮኖሚ ለማደግ በአዳዲስ የሥራ ዘርፍ ሊሠማሩ ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው በኛንጋቶም ወረዳ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓፓያ ምርት ከሁለት ዙር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።
የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት በዞኑ በሁሉም አካባቢ በሚባል መልኩ አመርቂ ምርት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው ፡፡
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ- ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ