በ2015 በጀት ዓመት ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በ2015 በጀት ዓመት ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2015 በጀት ዓመት ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ጽ/ቤቱ ሐምሌ 1 በይፋ የሚጀመረዉን የገቢ አሰባሰብን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጿል፡፡

የሌሞ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራዉ አለቃ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 86 ሚሊየን 612 ሺህ 400 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ  ከዕቅድ በላይ 116 ሚሊየን 732 ሺህ 530  ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡

ባለፋዉ ዓመት የተሰበሰበዉ ገቢ 69 ሚሊየን ብር እንደነበር የገለጹት አቶ ሽፈራዉ ዘንድሮ ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች የተቀናጀ ስራ በመስራታቸዉ የተሻለ ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰዉ ይህ ቅንጅታዊ አሰራር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አስረድተዋል።

በወረዳዉ በደረጃ ሐ 1ሺህ 251 ግብር ከፋዮች መኖራቸዉን የተናገሩት ኃላፊዉ በቀጣይ ከሀምሌ 1 ጀምሮ ለሚሰበሰበዉ ዓመታዊ የገቢ አሰባሰብ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንና ግብር ከፋዮችም በወቅቱ ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለባቸዉም አቶ ሽፈራዉ አሳስበዋል፡፡

የሌሞ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰልፋሞ ወ/ዩሐንስ እንዳሉት፤ ዘንድሮ ከሌላዉ ዓመት በተለየ መልኩ የንግድ ፍቃድ እድሳትና ምዝገባ በቴክኖሎጂ ተደግፎ እየተሰራ ነው።

በወረዳዉ 1ሺህ 691 ነጋዴዎች ፍቃዳቸዉን የሚያሳድሱ ሲሆን አዳዲስ ወደ ንግድ ስርዓት የሚገቡትም ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አቶ ሰልፋሞ ገልጸዋል።

የሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢዮብ ጩፋሞ በበኩላቸዉ የገቢ ጉዳይ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉም ርብርብ ማድረግ የሚገባው መሆኑን ጠቁመዉ ሐምሌ 1 በሚጀመረዉ የግብር አሳባሰብ ወቅት የተቀናጀ ስራ መሠራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የግብር ስወራና ማጭበርበርን ለማስቀረት እንደ ወረዳዉ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለፁት።

ወረዳዉ የሚያመነጨዉን ገቢ በአግባቡ ከመሰብሰብ አንፃር አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸዉን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪዉ በ2016 በጀት ዓመት ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የሊሣና እና የጀዌ ከተማ ታደጊ ማዘጋጃ ቤቶች ስራ አስኪያጆች የሆኑት አቶ አብርሃም ለምቤቦ እና አቶ ደምበሎ ጂካሞ በሰጡት አስተያየት ሐምሌ 1 በይፋ በሚጀመረዉ የአመቱ ግብር አሳባሰብ ሂደት የተሳካ እንዲሆን በንቃት እየሰሩ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን