አትሌቲክሱ ምን ነካው?

አትሌቲክሱ ምን ነካው?

በኢያሱ ታዴዎስ

ብዙም ሳላስለፋችሁ 2 ዓመታትን ብቻ የኋሊት ልመልሳችሁ፡፡ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 19 እስከ 27/2023 ድረስ በሀንጋሪዋ መዲና ቡዳፔስት ትልቁ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድግስ ተካሄደ፡፡

ወትሮ በአትሌቲክስ የማትታማው የመድረኩ ፈርጥ ኢትዮጵያ፣ በወንዶች 20 በሴቶች ደግሞ 22 በጥቅሉ 42 አትሌቶችን አሰባስባ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ትደምቅበት ዘንድ ቡዳፔስት ላይ ከተመች፡፡

የመካከለኛ፣ ረጅምና የማራቶን ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ነበረችና ልምድ ያላቸውን እንዲሁም ወጣቶቹን አትሌቶች መያዟ ጥሩ ውጤት እንደምታስመዘግብ ተስፋ ተጥሎባት ነበር፡፡ በሁለቱም ጾታዎች አትሌቶቹ በተወዳደሩባቸው ርቀቶች ብርቱ ፉክክር በማድረግ የሀገራቸውን ስም ለማስጠራት ተጋድሎ እንዳደረጉ የወቅቱ ውጤት ምስክር ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በእነዚህ ጀግኖች አትሌቶቿ ታግዛ አንጸባራቂ የሚባል ባይሆንም ምስጉን ስሟን የሚያስነሳ ድል አስመዘገበች፡፡ በአጠቃላይ 9 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ስትችል፣ 2 ወርቅ፣ 4 ብር እና 3 ነሐስ ሜዳሊያዎችን የግሏ አድርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ ሁለቱም ወርቆች በሴት አትሌቶቻችን ነበር የተመዘገበው፡፡ ጉዳፍ ጸጋይ በ10 ሺህ ሜትር እና አማኔ በሪሶ በማራቶን፡፡ ለተሰንበት ግደይ፣ ደርቤ ወልተጂ እና ጎይቲቶም ገብረስላሴ የብር ሜዳሊያ ሲያስመዘግቡ፣ እጅጋየሁ ታዬ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝታለች፡፡

በወንዶች ሜዳሊያ ውስጥ የገቡት 3 አትሌቶች ብቻ ነበሩ፡፡ ለሜቻ ግርማ ብር፣ እንዲሁም ሰለሞን ባረጋ እና ልዑል ገብረስላሴ ነሐስ፡፡ በዚሁ ዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ልዩ ክስተት የነበረው በ10 ሺህ ሜትር ጉዳፍ ጸጋይ፣ ለተሰንበት ግደይ እና እጅጋየሁ ታዬ ተከታትለው ከ1 እስከ 3 በመግባት ያስመዘገቡት ውጤት ነው፡፡ አረንጓዴ ጎርፍ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ስላለመቅረቱም ፍንጭ የሰጠ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሰበሰበችው 9 ሜዳሊያ ከዓለም 6ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ከኬኒያ በመቀጠል 2ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡

የቡዳፔስቱ ውጤት ኢትዮጵያ ከለመደችው አንጻር ዝቅ ያለ ቢሆንም አንገት የሚያስደፋ ግን አልነበረም፡፡ ቢያንስ 2 ወርቅ ተገኝቷልና፡፡

ከዚሁ በኋላ ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት አድርጋበታለች ወደ ተባለው የ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ነበር ያመራችው፡፡ በቡዳፔስቱ ዓለም ሻምፒዮና ያስመዘገበችውን ውጤት መነሻ በማድረግ የተሻለ ለማምጣት ዝግጅት ማድረጓ በኦሎምፒክ ኮሚቴው እና በአትሌቲክስ ፌደሬሽን በተደጋጋሚ መገለጹ ለኢትዮጵያዊያን ብሩህ ተስፋ ያጫረ ነበር፡፡

በዚህም ስነልቦና በመታገዝ በወንዶች 16 እና በሴቶች 18፣ በጥቅሉ 34 አትሌቶችን በመያዝ ነበር ለውድድር የቀረበችው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተጠበቀው ልክ ግን መሆን አልቻሉም፡፡

በአጠቃላይ የሰበሰቡት 4 ሜዳሊያዎችን ብቻ ነበር፡፡ 1 የወርቅ እና 3 የብር ሜዳሊያ። ብቸኛዋ ወርቅ በአትሌት ታምራት ቶላ በማራቶን ነበር የተገኘችው፡፡ በሪሁ አረጋዊ፣ ጽጌ ዱጉማ እና ትዕግስት አሰፋ ደግሞ የብር ሜዳሊያ ባለቤቶች ሆነዋል፡፡

ይህም ማለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር በክብር ከፍ ብሎ የተሰማው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። ታምራት ቶላ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያውን በተረከበበት ወቅት፡፡ ውጤቱም ኢትዮጵያዊያኑን በእጅጉ ያስከፋ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለውጤት ማጣቱ እርስ በርሳቸው ጣት እየተቀሳሰሩ ኃላፊነት ላለመውሰድ ሽሽትን ሲመርጡ ትዝብት ውስጥ መግባታቸው አይዘነጋም፡፡

የፓሪሱም ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ክብሯን ከፍ ከማድረግ ይልቅ አትሌቲክሷ ቀስ በቀስ ቁልቁል እያሽቆለቆለ ስለመሆኑ የአደጋ ምልክት የሰጠ ነበር። ቀይ መብራት በሚያስብል ደረጃ፡፡ ከዚህ በኋላ ለአትሌቲክሱ የውድቀት ጉዞ ምክንያት ተደርጎ የነበረው የፌደሬሽኑ አመራር በሙሉ ለውጥ ተደረገበት፡፡

ስለሺ ስህን ፕሬዝደንት፣ ገዛኸኝ አበራ ምክትል ፕሬዝደንት እና ቢልልኝ መቆያ ዋና ጸሃፊ በመሆን ተሾሙ፡፡ ይህ የአመራር ስብስብ ከተመረጠ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ለቀጣዩ የ2025 የቶክዮ ኦሎምፒክ ተዘጋጅቶ አትሌቶችን ማቅረብ ግድ ሆነበት፡፡

አትሌቲክስ ፌደሬሽኑም በየርቀታቸው ሚኒማ ያሟላሉ ያላቸውና ለውድድሩ ብቁ እንደሆኑ ያመነባቸውን 16 ወንዶች እና 20 ሴቶች፣ በጥቅሉ 36 አትሌቶችን ነበር ይዞ ወደ ቶክዮ የከተመው፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተወዳደሩባቸው ርቀቶች ውጤት ለማምጣት የየግል ጥረታቸውን ቢያደርጉም ስኬታማ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 2 ብር እና 2 ነሐስ፣ በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎችን ብቻ ነበር ያሳካችው፡፡

በውድድሩ ከወርቅ ሜዳሊያ ጋር ሆድና ጀርባ ሆና ምንም ሳታሳካ ተመልሳለች፡፡ ቶክዮም በአደባባዮቿ በክብር ከፍ ሳታደርጋት ሸኝታታለች። ብቻ የቶክዮው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ውጤት ርቋት የሃዘን ማቅ ለብሳ የተመለሰችበት ሆኗል፡፡

አስቡት እንግዲህ በሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት ወርቅ ከማግኘት ወደ ምንም ስትሸጋገር። በቡዳፔስቱ ዓለም ሻምፒዮና 2 ወርቅ ከተገኘ በኋላ፣ በፓሪስ ኦሎምፒክ 1 ወርቅ ወደ ማግኘት ተሸጋገረና ቶክዮ ላይ ጭራሽ ያለ ወርቅ ወደ መመለስ በቃች፡፡

አሁን በእርግጥም የቶክዮው ውጤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቀይ መስመር ውስጥ ስለመግባቱ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከቶክዮ መልስ አትሌቶችና አሰልጣኞች ለውጤት ቀውሱ ምክንያት ያደረጉት የአትሌቶች የቡድን ሥራ እጅግ አናሳ መሆንና ተነሳሽነት እጥረት መሆኑን ነው፡፡

በምክንያትነት የተጠቀሰው ትክክል ቢሆንም ውጤት በጠፋ ቁጥር ይህ መሆን አልነበረበትም፣ እንዲህ መደረግ ነበረበት ማለቱ አሁንም ከኃላፊነት ለመሸሽ የሚሰጥ አስተያየት ያስመስላል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከውጤት እየራቀ ስለመምጣቱ ምልክት ካየን እኮ ቆይተናል። በተለይም በኦሎፒክ መድረኮች እንደ ቀድሞው በወርቅ መንበሽበሽ እየቀረ መጥቷል፡፡ ዓለም ሻምፒዮናውም ቢሆን በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑን ከዘንድሮው የቶክዮ በላይ የተሻለ ማሳያ መድረክ የለም፡፡

አሁን አሁንማ የአትሌቲክሱ ውድቀት እንደ እግር ኳሱ እንዳይሆን ስጋት መደቀኑ አልቀረም። ከዓመት ዓመት ይነሳል እየተባለ ሲጠበቅ ይባስ ወደ ኋላ ከማሽቆልቆል አላለፈም፡፡ አትሌቶችም የማሸነፍ ሞራላቸው በእጅጉ ተቀዛቅዟል፡፡

የሚገርመው ደግሞ አትሌቶቹ ብቃታቸው ወርዶ ነው እንዳይባል በግል በሚያደርጓቸው ውድድሮች በየርቀቱ ቀዳሚ ሲሆኑ እንመለከታለን። ይሄ ውጤታቸው በሚኒማ ተመዝኖ ነው ስኬታማነታቸውን በሀገር ደረጃ እንዲደግሙት ታምኖባቸው ዕድል የተሰጣቸው፡፡

እንደ ኦሎምፒክ እና ዓለም ሻምፒዮና ያሉ ሀገራዊ ግዳጆች ላይ ግን አቅም የሚከዳቸው ይመስል ሀገራቸውን የሚያስጠራ ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት የዛሬውን ሳይሆን የቀድሞውን በእነ ሐይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ የመሳሰሉ ፈርጥ አትሌቶች ዘመን የመጣውን ድል እንደ ታሪክ ለመዘከር ተገድደናል፡፡

ውጤቱ ካልተስተካከለ ደግሞ ታሪክ ብቻ እያወሱ መኖሩ ልማድ ሆኖ ሊቀር እንደሚችል መገመቱ ቂል አያስብልም፡፡

አሁን ባለው ደረጃ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ለውጤት ማጣቱ እንደ ሌሎቹ ጊዜያቶች አትሌቶችና አሰልጣኞች ወይም ደግሞ የሚመለከታቸው የስፖርቱ አመራሮች ላይ ጣት እየቀሰሩ ተጠያቂ ማድረግ ፋይዳ እንደሌለው የትናንት ተሞክሯችን ትምህርት የሰጠን ይመስለኛል፡፡

አሁን የሚያስፈልገው አትሌቲክሱ በእርግጥም አደጋ ላይ መውደቁን አምኖ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ደፋ ቀና ማለቱ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ አትሌቲክሱን ከሚመሩት የሚመለከታቸው አካላት ጀምሮ አሰልጣኞች እና አትሌቶች ያለልዩነት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይሄ እርምጃ ሕመም ውስጥ የገባውን አትሌቲክስ ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጎ ዳግም ኢትዮጵያን በዓለም የስፖርት አደባባዮች በክብር ከፍ ማድረጉ አይቀርም፡፡