የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምርምር የተረጋገጡ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምርምር የተረጋገጡ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 28/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምርምር የተረጋገጡ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ከወራቤ ምርምር ማዕከል የተገኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው በሄክታር እስከ 84 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ አርሶአደሮች ተናግረዋል::

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም በኩታ ገጠም የለማ የበቆሎ ማሳ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።

አርሶ አደር አህመድን አስፋን እና መሃሙድ አስፋን በአበሽጌ ወረዳ ቦቀታና ሰሪቴ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የበቆሎ ምርጥ ዘር በኩታ ገጠም በክላስተር መዝራታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በሄክታር እስከ 84 ኩንታል እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኮሙኒኬሽን ምርምር ዳይሬክተር አቶ አብድራዛቅ አብደላ የምርምር ማዕከሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩ የምግብ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የተሻሻሉ የቢ-ኤች-549 የበቆሎ ምርጥ ዘር የማስተዋወቅ ስራ አየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በኩታ-ገጠም የለማው በቆሎ ማሳ በሄክታር 84 ኩንታል በላይ ምርት የሚያስገኝ መሆኑንም አቶ አብዱራዛቅ ጠቅሰዋል።

የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቀድራላ ዋበላ እንደገለፁት ማዕከሉ በ6 የምርምር ዘርፎች የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በምርምር የታገዙና የተሻሻሉ የእንስሳትና የሰብል ዝርያዎችን በስፋት ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ዶክተር ቀድራላ አመልክተዋል።

ቢሮው ከኢንስቲትዩቱ ጋር የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመፍታት የምርምር ስራዎች ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊና የእርሻና ሆልቲ ካልቸር ሰብሎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓለምይርጋ ወልደስላሴ ናቸው።

በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦት ማሻሻል እንዲሁም የአርሶ አደሩንና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ኢንስትቲዩት ዋና ዳሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ በበኩላቸው በምርምር የታገዙ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ በዘርፉ የክልሉን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በሽታ የሚቋቋሙ ፣የወተትና የሰብል ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ እና ሀገረ ሰብ ዝርያዎችን የሚያሻሽሉ ከ200 በላይ የሆኑ ምርምሮች በማዕከሉ እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ፀጋዬ አመልክተዋል።

የግብርናው ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚው ማንሰራራት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ያሉት አቶ ፀጋዬ BH-549 የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ለአርሶ አደሮች በስፋት በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን