የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት ከደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ሕፃናት መምሪያ ጋር በመተባበር “የዎና ናና” የህፃናት ልማት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በዲመካ ከተማ ተካሂዷል

የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት ከደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ሕፃናት መምሪያ ጋር በመተባበር “የዎና ናና” የህፃናት ልማት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በዲመካ ከተማ ተካሂዷል

የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ጎባ ኛላማይ በዞኑ በማወቅም ሆነ ከግንዛቤ እጥረት የሚፈፀሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች የነበሩ ቢሆኑም አብዛኛው ውሳኔ አግኝቶ እንዲቀር ተደርጓል ብለዋል።

በአካባቢው “ሚንጊ” ወይም ሕፃናት ሲወለዱ የላኛው ጥርስ ቀድሞ ከበቀለ እንደ መጥፎ ክስተት ወይም በአካባቢው ባለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የተዛባ አመለካከትን በመያዝ በማህብረሰቡ ዘንድ ተገለው ሕይወታቸው ላይ ጭምር ጉዳት እንዲደርስ ይደረግ እንደነበር የመምሪያ ሀላፊዋ አብራርተዋል።

ሆኖም ይህ አመለካከት ተከታታይነት ባለው ግንዛቤና በሀገር ሽማግሌዎች እና በጎሳ መሪዎች ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማስቀረት ተችሏል ሲሉ ወ/ሮ ጎባ አስረድተዋል።

“ሚንጊ” ተብሎ ለዘመናት ሲጠራ የነበረው ስያሜ “ዎና ናና” ወይም የእኛ ልጆች የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶ የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት እየሠራ ያለው ተግባር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ናቸው።

የትኛውም ዜጋ ከወሊድ ጋር በተያያዘም ይሁን በማንኛውም ባህል ተፅእኖ ምንም ዓይነት ማግለልና ሰብአዊ ጥቃት ሳይደርስባቸው የመኖር መብታቸው ሊከበር ይገባል ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት “ዎና ናና” በሚል ፕሮጀክት በማቋቋም በአካባቢው ባህል የሚገለሉና ጥቃት የሚፈፅምባቸው ልጆቸ ከወላጆቻቸው ጋር መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የትምህርት፣ የጤናና መሰል ሌሎች ድጋፎችን በማመቻቸት ችግሩ እንዲወገድ እየሠራ መሆኑን የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ወ/ሮ ማዛሮት ኦሪዮን ገልፀዋል።

“ሚንጊ” ተብሎ ጥቃት የሚደርስባቸው ሕፃናት በተለይ በበናፀማይና በሐመር ወረዳዎች የሚፈፀም ሲሆን ድጊቱን የማስቀረት ተግባር አንዱ ከሌላው ልምድ በመቅሰም በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ በመድረኩ የተገኙ አካላት አረጋግጠዋል።

“ዎና ናና” የሚለው ስያሜ ከበናፀማይ ወረዳ ባሻገር እንደዞን በሁሉም አካባቢ ስያሜው ተግባራዊ እንዲደረግ በልዩ ትኩረት መሠራት አለበት ሲሉም የጋራ አቋማቸውን ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

በየአካባቢው ባሉ ቀዳሚ የጎሳ መሪዎች ወይም በአካባቢው አጠራጣር በባላባቶች ውሳኔ ጥቃት ሊደርስባቸው የነበረ በርካታ ሕፃናትን መታደግ ተችሏል ተብሏል በመድረኩ።

በመድረኩ የተገኙ ቀዳሚ የጎሳ መሪዎችም ከዚህ በፊት በማወቅም ሆነ ከግንዛቤ እጥረት በልጆቻችን ላይ ያደረስነውን ጥቃት ፈጣሪ ይቅር እንዲለንና ድርጊቱ ፈፅሞ እንዳይፈፀም እየሠራን ሲሆን ከዚህ በኋላ በየትኛውም መልኩ “ሚንጊ” ተብሎ የሚፈፀም ጥቃት እንዳይኖር በሀላፊነት እንሠራለን ብለዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን