የሌማት ትሩፋት ውጤታማነት ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ የአከባቢውን ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱ ተገለጸ

የሌማት ትሩፋት ውጤታማነት ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ የአከባቢውን ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱ ተገለጸ


ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሌማት ትሩፋት ውጤታማነት ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ የአከባቢውን ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱን በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ፡፡‎

የሚዛን ግብርናና ስልጠና ኮሌጅ በተለያዩ የሞያ መስኮች አጫጭር ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ብዜት ላይ በመስራት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን የእንስሳት ሳይንስ መምህርና የኢንተርፕራይዝ እርሻ ልማት ስራ አስኪያጅ መ/ር ዋለልኝ አለምነህ ይናገራሉ፡፡

‎በአዲሱ የመንግስት እሳቤ የአከባቢውን ማህበረሰብ ይዞ የሚወጣበትና ሰራተኛውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂ ንግድ እና የፈጠራ ሀሳብን በማመንጨት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከመንግስት ድጎማ በጀት ለመውጣት በስራና ክህሎት ሚኒስተር ስር በኢንተርፕራዝ ተደራጅቶ ስራ መጀመሩን ነው መ/ር ዋለልኝ የገለፁት ።

‎በዋናነት በእንስሳት ዘርፍና በሰብል ልማት ላይ እንደሚሰራ የገለፁት መ/ር ዋለልኝ እነዚህም በዶሮ እርባታ የወተት ከብት እርባታና የንብ ማነብ ላይ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ።

‎በዶሮ እርባታ 8ሺ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች መኖሩን እና እንቁላል መጣል መጀመራቸውን የገለፁት መ/ር ዋለልኝ ይህ ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል ።

‎ በተያዘ በጀት ዓመት የስጋ እና የእንቁላል ጫጩቶችን በማስፈልፈል ለማህበረሰቡ ከማሰራጨት ባለፈ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ላይ ለመስራት በዕቅድ ደረጃ መያዙን ተናግረዋል።

‎በ2017 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 4 ሚሊዬን ብር ወጪ በማድረግ 10 ጊደሮችን ግዢ በመፈፀም በሰው ሰራሽ በማዳቀል ወደ ስራ መገባቱን የገለፁት መ/ር ዋለልኝ 7ቱ ምርታማ ለመሆን መቃረባቸውን ተናግረዋል ።

በንብ ማነብ 400 ዘመናዊ ቀፎዎች በቂጤ ጣቢያ መኖሩን ተናግረው በሩብ ዓመቱ ተጨማሪ 40 ዘመናዊ ቀፎውችን ወደ ኮይ የልማት ጣቢያ ላይ በመስቀል የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል ።

‎በባለፈው 2017 ኮይ ቀበሌ ላይ 200ሄ/ር መሬት በመረከብ 37 ሄ/ር መሬት ለሰሊጥ እርሻ በማዋል በሄ/ር 6 ኩ/ል አጠቃላይ 200 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የገለፁት መ/ር ዋለልኝ በተመሳሳይ በቆሎ 15.5ሄ/ር መሬት ላይ በመዝራት ምርቱ በመሰብሰብ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ከ600ኩ/ል በላይ ምርት ይገኛል ብለዋል ።

‎በቀጣይም ኮሌጁንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ተልዕኮ ተይዟል ያሉት መ/ር ዋለልኝ፥ የሻይ ልማት ወደ ተግባር ለመግባት የዞንና የክልል መንግስት ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረው ቀሪ የችግኝ የማባዛት ስራ ነው ብለዋል።

‎በተያዘው 2018 በጀት ዓመት ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ጅምር ስራዎችን በማጠናከር ችግር ፈቺ በሆኑ መስኮች ላይ በጥናት በማስደገፍ ኮሌጅ ተልዕኮውን ለማሳካት ይሰራል ብለዋል ።
ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብሬኤል – ከሚዛን ቅርንጫፍ