የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ለ28ኛ ዙር በመደበኛ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን እጩ መምህራን በዲፕሎማና በሰርተፊኬት ደረጃ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ አስመርቋል

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ለ28ኛ ዙር በመደበኛ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን እጩ መምህራን በዲፕሎማና በሰርተፊኬት ደረጃ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ አስመርቋል

ሀገርንና ትውልድን ለመቅረፅ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የመምህራን ሚና ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ገልጸዋል፡፡

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከተመሰረተ 49 ዓመታት እንዳስቆጠረ የተናገሩት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ንጋቱ ቱአሻ፤ በዚህም በርካታ ንቁ መምህራን በማፍራት ለሀገር አበርክቷል ብለዋል።

አንጋፋ የሆነው የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ብቁና ትውልድን የሚገነቡ መምህራን እያፈራ ይገኛል ሲሉ አክለው ገልፀዋል።

በ2018 ዓ.ም በ28ኛው ዙር በመደበኛ መርሃ ግብር ካሰለጠናቸው አጠቃላይ ተመራቂ እጩ መምህራን ውስጥ 348 ወንድ እና 142 ሴት በጠቅላላው 490 መሆናቸውን የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ንጋቱ ቱአሻ ተናግረዋል።

የትምህርት ስብራትን ለማከም ባለፉት ዓመታት ከቅድመ አንደኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ተናግረዋል።

በዚህም ሀገርንና ትውልድን የሚገነቡና የሚቀርፁ መምህራን በማፍራት እንገኛለን ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተመረቁ እጩ መምህራን በኮሌጁ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ሀገራቸውንና ቤተሰባቸውን በታላቅ ኃላፊነት እንዲያገለግሉ አቶ በየነ በራሳ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ፣ የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሉ አዱላ፣ የሲዳማ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ወይነሸት መንገሻ፣ የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ንጋቱ ቱአሻ፣ የኮሌጁ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ዲን ዶ/ር ደረጀ ዳቃሞ፣ ተመራቂ መምህራን እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ጠቅልል ቀድሩ