ከ2 ሺህ 600 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እናቀርባለን – የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ

ከ2 ሺህ 600 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እናቀርባለን – የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ

‎ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ2 ሺህ 600 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እንደሚሰራ የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

‎በዞኑ ያለው የቡና ሽፋን ከ19 ሺህ 600 በላይ ሄክታር ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ11 ሺህ 200 በላይ ሄክታር መሬት ላይ ያለው ቡና ምርት የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።

‎በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ዩኒት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሸናፊ ጃሌ የዘንድሮ የእሸት ቡና ግብይት ለመጀመር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።

‎ከአርሶ አደር ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላትና በቡና ግዢ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በተለይ የቡና ጥራትን በሚመለከት የተለያዩ መድረኮች በመፍጠር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ከ2 ሺህ 200 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አሸናፊ፥ ዘንድሮ ጥራቱን የጠበቀ ከ 2 ሺህ 600 ቶን የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው ብለዋል።

‎የሚፈለገውን ገቢ ከቡና ለማግኘት ለቡና ጥራት ቅድሚያ መስጠት ወሳኝ በመሆኑ ከቡና ለቀማ ጀምሮ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
‌‎
‎ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን