“የባህር በር የህልውና ጥያቄ ነው”

“የባህር በር የህልውና ጥያቄ ነው”

በምንተስኖት ብርሃኑ

ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን እንደምን ከረማችሁ? ባሳለፍነው ሳምንት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) “የመደመር መንግስት” የተሰኘው አራተኛ መጽሐፋቸው መመረቁ ይታወሳል፡፡ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) “በድጋሚ ወደ ቀይ ባህር መመለስ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በማንሳት መሳካቱ አይቀሬ” ነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ “ዛሬ የኛ የሆነውን ቀይ ባህር መልሶ ለመጠየቅ የሚሰጋ፣ የሚጠራጠር ትውልድ መፈጠሩ የስነልቦና ስብራት አካል ነው፤ አንችልም ብሎ ነው የሚያስበው፤ እኔ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ኢትዮጵያ ትችላለች” ሲሉ ኢትዮጵያ የመውጫና መግቢያ በሯን /የባሕር በር/ ማበጀቷ አይቀሬ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

“ኢትዮጵያን የሚያልክ ሀገር የባህር በር ሳይኖራት ለልጆቻችን መሸጋገር አለበት ብሎ ማመን ተገቢ እሳቤ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ “ይሄን ለማሳካት (ባህር በርን) ውጊያ፣ ግጭት ያስፈልጋል ብለን አናምንም፤ ለዚህም ነው ለ5 ዓመት ስንለማመጥ የነበረው” ብለዋል።

“አሁንም በሰላም በዓለም ህግ መሰረት ኢትዮጵያን ከዘጋት በር እና ድሃ ካስባላት መጠሪያዋ መገላገል አለባት ብለን ስለምናምን በየትኛውም መድረክ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር የሚፈቅድ አካል ካለ እጃችን ከምን ጊዜውም በላይ የተዘረጋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ የጂዮግራፊ እስረኛ ሆና ለዘላለም ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ካለ እርሱ የሞተ ነው፤ ሰላም ታስቀድማለች፤ ድህነትን ትፋለማለች መውጫ መግቢያ በሯን ታበጃለች፤ ይህ አይቀሬ ጉዳይ መሆኑን ተገንዘበው ወንድም እህቶቻችን በፈጠነ ጊዜ ለድርድር እራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው” ሲሉም ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እኔም በሃሳባቸው እስማማለሁ፡፡ የባህር በር ጉዳይ በአንድ ሀገር የዕድገት ስትራቴጂ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው እንደመሆኑ የዛሬው የሃሳብ-አለኝ ጉዳዬ ማጠንጠኛ ይሆን ዘንድ መርጬ እነሆ የግል ምልከታዬን ላጋራችሁ ወድጃለሁ፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን የባህር በር ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንደምታ አኳያ የባህር በር አልባ ለሆኑ ሀገራት ይዋል ይደር እንጂ ትልቅ ሃገራዊ አጀንዳ መሆኑ አይቀርም፡፡

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ያሉ ሀገራት፣ የጀመሩትን ልማት በማስቀጠል የሕዝቦቻቸውን የዕለት ተዕለት ሕይወት ለማቅለልም ሆነ የመልማት ፍላጎታቸውን ተጨባጭ ለማድረግ የባህር በር ጉዳይ ወሳኝም፣ የሕልውና ጉዳይም መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ይሄን መነሻ በማድረግም ኢትዮጵያ ያቀረበችው እና በዲፕሎማሲ መንገድ ተጉዛ ምላሽ ለማግኘት እየሰራች ያለበት የባህር በር ጥያቄ ታዲያ፤ ከሞራልም ሆነ ከአለም አቀፍ ህግ አኳያ ተገቢነት ያለው በአግባቡ እና በልኩ ሊተረጎም የሚገባው የመብት ጥያቄ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመናት ከአንድም በላይ የሁለት እና ሶስት ወደቦች ባለቤት በሆነችባቸው የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ አልፋለች፡፡ በእነዚህ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የባህር በር ባለቤትነቷ የነበረው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ፈጥሮት የነበረው የስነልቦና ከፍታ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ይህችው ሀገር በሌላ የታሪክ አጋጣሚ ያሏትን የባህር በሮች በሙሉ አጥታ፤ የገቢና ወጪ ንግዷን እንኳን ለማከናወን የሌሎችን ወደብ ለመጠቀም የተገደደችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው ከባህር በአጭር ርቀት ላይ እያለች ፈጣን እና ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎት የምታገኝበት እድል አጥታ መቆየቷ ነው፡፡ ይህም በሕዝቦቿ የመልማት መብት እና ጥያቄ ላይ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ዘመን፣ የመልማት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ የመሆኑን ያህል፤ የባህር በር ጉዳይም ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያ በተመሳሳይ መልኩ የህልውና ጉዳይ ሆኗል። በተለይ ለአኛ ለኢትዮጵያዊያን አሁን ለመልማት ካለን መሻት እና መሻታችን ከወለደው መነቃቃት አኳያ የባህር በር ጥያቄያችን አጠቃላይ የህልውና አጀንዳችን መደረጉ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡

የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ሆነ ማለት ደግሞ፤ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እጣ ፈንታቸው ለተሳሰሩት የአካባቢውም ሆነ ለቀጠናው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርተው አቅምን በጋራ ደምሮ በጋራ የመልማት እሳቤን መላበስ የግድ ይላቸዋል ማለት ነው፡፡

ምክንያቱም የእነዚህ ሕዝቦች ውድቀትም ሆነ መነሳታቸው፤ ድህነትም ሆነ ብልጽግናቸው በአብሮነታቸው ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩን አቅልሎ የአንድ ሀገር አጀንዳ አድርጎ ማየትና ለጉዳዩ ያልተገባ ትርጓሜ መስጠት ተገቢና አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡

በተለይ በአንዳንድ ሀገራት እንደሚታየው ጥያቄውን የሀገር ውስጥ ፖለቲካ አጀንዳ ከማድረግ ጀምሮ፤ የጣልቃ ገብነት መልካም አጋጣሚ አድርጎ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ይሄን እያደረጉ ያሉ ሀገራት አካሄዳቸው የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች ወንድማማችነት እና ከዚህ የሚመነጭ አብሮ የማደግ ፍላጎትን ታሳቢ ያላደረገ፤ ድርጊታቸውም አካባቢውን ለተጨማሪ ግጭት የሚዳርግ ነው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷን የሚመጥን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ እንደ ስህተት ሊታይ አይገባም፡፡ ጥያቄዋ በአካባቢው ለሚገኙ የወደብ ባለቤት ለሆኑ ሀገራት በሙሉ የቀረበ እንደመሆኑ፤ በቀጠናው ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ በአካባቢው አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ተጨባጭ ተሞክሮ መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

የአካባቢው ሀገራት ይህን አዲስ የትብብር ምዕራፍ፤ ለሕዝቦቻችው የመልማት ፍላጎት እንደመልካም አጋጣሚ ሊወስዱት፤ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ትልቅ አቅም አድርገው በቅን መንፈስ ሊረዱት እና ለተግባራዊነቱ እራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡

ከዚህ ውጪ የሀገሪቱን የባህር በር ጥያቄ በእልህ እና በማን አለብኝነት፣ በግትርነት እና በጠላትነት መንፈስ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ላለማስተናገድ የሚደረግ ጥረት ስህተት በመሆኑ ተገቢውን ዲፕሎማሲዊ ሥራ በማከናወን ለማረም መሥራት ከመንግስት ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ መነሻ አድርገው የሚታዩ ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች፤ ከቅኝ ግዛት እሳቤ እስራት እና በቀጠናው ላይ ውጥረትና ግጭትን ከመጋበዝ በጸዳ መልኩ፤ የቀጠናውን ወንድማማች ሕዝቦች አቅምን አሰባስቦ የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ጥያቄውን በኃላፊነት መንፈስ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችል ዝግጁነት እንዲፈጥር ያልተቋረጠ የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶ/ር) እንዳሉት ትውልዱ ከአይቻልም መንፈስ በመላቀቅ ለሃሳቡ ስኬት የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምክንያታዊና ፍትሃዊ ነው። በመሆኑም ሕዝቡ የሃሳብ ልዩነት እንኳን ቢኖር የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ተፈፃሚ እንዲሆን የሚጠበቅበትን የዜግነት ግዴታ ሊወጣ ይገባል፡፡

ይህን ማድረግ ከተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የባህር በር ጥያቄን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞቻችን የሚያስከብሩ ጉዳዮችን በማሳካት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችንን ከድህነት ማላቀቅ ይቻላል እና ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ሚና እንወጣ እያልኩ የዛሬን አበቃሁ፡፡ ቸር ይግጠመን!