ታሪክ ራሱን ደገመ

በኢያሱ ታዴዎስ

ልክ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቁ ከተበሰረበት ዕለት ጀምሮ ሀገሪቱን የደስታ ማዕበል አናውጧታል። ከተሞች በዚሁ የደስታ ማዕበል ውስጥ በሰጠሙና ይህንኑ ስሜታቸውን በአደባባይ በመፈክር ጭምር በሚገልጹ ሰዎች ተጥለቅልቀዋል፡፡

በገጠራማ አካባቢዎችም ይኸው ደስታ ተስተጋብቷል፡፡ የዘመናት ሕልሙ የተሳካለት ሕዝቡ ሁሉ ወደ አደባባይ እየወጣ “እንኳን ደስ አለሽ ሀገሬ፤ ሕልምሽ እውን ሆኗል” በማለት ደስታው ላይ ጭፈራ አክሎበት ስሜቱን ገልጿል፡፡

ብቻ ጳጉሜ ወር መጨረሻ እና መስከረም ወር መጀመሪያ ለኢትዮጵያ ልዩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ወጥኖ ማሳካት፣ ዘርቶ መቃም፣ ጸንሶ ወልዶ ለቁም ነገር ማብቃት መሆኑን የህዳሴ ግድብ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

ዓለም ከድህነት ወለል በታች እንደሆንን በመቁጠር ከድርቅና ረሃብ ጋር እያቆራኘን መሳለቂያ አድርጎን እንደነበር መቼም የማይዘነጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት መቻል መሆኑን ማንም አልተረዳም ነበር፡፡ ታሪክ ብቻ ተሸክመን በድህነት አለንጋ እየተገረፍን የምንባዝን ምስኪኖች ተደርገንም ነበር፡፡

ግን እኮ ታሪክ በባህርይው ራሱን ይደግማል፡፡ የትናንት ጀግንነትና ሥልጣኔ ጊዜውን ጠብቆ መገለጡ አይቀርም፡፡ ታሪክ ታሪክ ብቻ ሆኖ አይቀርም፡፡ መልኩን ቀይሮ እንደ አዲስ ብቅ ይላል፡፡ ከመወሳት ባሻገር ዛሬ ላይ ክስተት ሆኖ ይመጣል፡፡

ጀግንነትና ሥልጣኔ ከተነሳ ደግሞ ማን እንደ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ እኮ ጀግንነትንም ሆነ ሥልጣኔን ትናንትና በታሪክ አጣጥማቸዋለች። እንደ ዛሬው ሀገራት 195 ሳይሆኑ በፊት፣ ኢትዮጵያ ቀደምት ሆና ሥልጣኔን ከመሰረቱ ጥላለች፡፡ በንግድ ቢባል፣ በግሩም የግንባታ ንድፎች፣ ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤ በመከተል፣ አስደማሚ ኪነሕንጻዎችን በመገንባት፣ በዕደ ጥበብ፣ ብቻ በብዙ ዘርፎች ኢትዮጵያ ቀዳሚ ነበረች፡፡

ጥንታዊያኑ አክሱምና ላሊበላ ውቅር ሕንጻዎች፣ የፋሲለደስ ግንብ፣ ጢያና ቱቲ ፈላ ትክል ድንጋዮች፣ ዛሬም ድረስ አስደማሚ ገጽታ ያላቸው ቤተመንግስታት፣ የተለያዩ ማራኪ ውበት የተጎናጸፉ አልባሳትና ጌጣ ጌጦች፣… ምን ቅጡ… ግሩም የኢትዮጵያዊያን እጆች ውጤት ናቸው፡፡

በጀግንነትም ቢሆን የትኛውም በቁጣ ተነስቶ ኢትዮጵያን በጦርነት የወረረ ኃይል ድል ነስቷት አያውቅም፡፡ የተቃጡ ጦርነቶች በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ድል ነሺነት ተቋጭተዋል፡፡ ለጠላቶቿ ተበግራ አታውቅም።

ለዚህም በ1550ዎቹ ከቱርክ፣ በ1830ዎቹና 40ዎቹ ዳግም ከቱርክ፣ በ1870ዎቹ ከግብጽ፣ በ1880ዎቹ ከማህዲስት (ሱዳን)፣ የመጀመሪያውና ሁለተኛው ከጣሊያን፣ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት መጠናቀቃቸው ማሳያ ነው፡፡

ታዲያ ያ ሁሉ ሥልጣኔ እና ጀግንነት ግን በጊዜ ሂደት የተረሳ ይመስል ነበር፡፡ ኢትዮጵያን አሳንሶ የማየት አባዜ የተጠናወታቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ድህነቷንና ኋላ ቀርነቷን እያነሱ መቼም እንደማትነሳ አድርገው የቆጠሯትም ቁጥራቸው አያሌ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ግን እንደዚያ አይደለችም። የቅርብ ጊዜ ታሪኳ እንኳን ታላቅነቷን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የአባይን ወንዝ ተጠቅማ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ለመገንባት ስትነሳ ሊያደናቅፋት ያልተነሳ ኃይል አልነበረም፡፡

ጦርነት እስከማወጅ ድረስ እንደ ግብጽ ያሉ ባላንጣዎቿ እያስፈራሩ ሊያሸማቅቋት ሞክረዋል፡፡ በውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ከባላንጣዎቿ ጋር አብረው ለማፈራረስ እዚህም እዚያም ጉድጓድ ምሰዋል፡፡

ታዲያ ከዚህ መነሻ በተለይም በውስጥ ግጭቶች ሲበራከቱ ኢትዮጵያ አብቅቶላታል ተብሎም ነበር፡፡ በዚያ ላይ በውጭም በኩል በግብጽ አጋፋሪነት ኢትዮጵያን የሚቃረኑ ጎረቤት ሀገራት መነሳታቸው ሌላው ከባዱ ፈተና ነበር፡፡

በአንድ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ የጦርነት ደመና ማንዣበቡም የዚሁ ምልክት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጀግንነት ግን ጠላትን በመሳሪያ ኃይል ማንበርከክ ብቻ አልነበረም፡፡ ጥበባዊ የተሞላ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድንም ታውቅበታለች፡፡

ለዚህም ሶማሊያ እና ጂቡቲ በግብጽ ግፊት ከኢትዮጵያ ጋር ቁርሾ ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያ በተከተለችው ሰላማዊ የዲፕሎማሲ አካሄድ ሊፈታ መቻሉን አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡ በተለይም ሶማሊያ በወደብ ምክንያት ኢትዮጵያን ስታኮርፍ ግብጽ ወደ ጦርነት እንድትገባ የመሳሪያ ድጋፍ ሁሉ አድርጋ “ፈረሱም ሜዳውም ያው” በማለት ከልክ ያለፈ ግፊት ስታደርግ ነበር፡፡

ይሄኔ ኢትዮጵያ ልትመክተው የማትችለው ጦርነት ውስጥ መግባቷ አይቀሬ እንደሆነ ተገመተ፡፡ በሂደት ግን የታሰበው ሳይሆን ቀረና ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወደ ሰላማዊ መድረክ መጥተው ለመጨባበጥ በቁ፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ለመቀነስ ሁነኛ መሳሪያ ሆኗታል፡፡ አሁንም ቢሆን ግብጽ እና ሱዳን ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ ራሳቸውን በባላንጣነት ከማየት አልተቆጠቡም። ይሄ ግን ኢትዮጵያ ያሰበችውን የብልጽግና ጉዞ ከማድረግ የሚያቆማት አልሆነም፡፡

ግዙፉን የሕዳሴ ግድብ በስኬት ገንብታ እንድታጠናቅቅ ያስቻላት ይኸው ቆራጥነቷ ነው፡፡ ከውጭ ከሚገኝ እርዳታ ወይም ነጻ ሥጦታ አልነበረም ግድቡ የተገደበው። በራሳቸው በኢትዮጵያ ልጆች ወዝና ደም እንጂ፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን ጀምሮ ለመጨረስ የዓለም መንግስታት ይረዷት ዘንድ ምጽዋት አልለመነችም፡፡ አነሰኝም ብላ ደጅ አልጠናችም፡፡ በአንጻሩ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው የገዛ ዜጎቿን በውስጥም በውጭ በደቦ ውጥኗን ያሳኩላት ዘንድ ጥሪ ማቅረብን ነው የመረጠችው፡፡

የእሷን ጥሪ ሰምቶ አሻፈረኝ ያለ ዜጋ አልነበረም፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ አቅም ከሌለው እስከ ባለሃብት ለእናት ሀገሩ የቋጠራትን ጥሪት ሳይቀር ሳይሰስት ያልሰጠ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በሀገር ውስጥ ያለም ሆነ በውጭ የሚገኝ ዳያስፖራ ሁሉ “ግድቡ የእኔ ነው” በማለት በገዛ ገንዘቡ ሕዳሴ ግድቡን ገንብቷል፡፡

ታዲያ ከዚህ በላይ ኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ፍቅር፣ መተባበር፣ ጀግንነት እና ቆራጥነት መሆኑን ምን ማሳያ ሊኖር ይችላል። ጦርነትንም ቢሆን ያውም በዚህ ዘመን ሕወሓት በከፈተበት ጊዜ በአንድነት በመነሳት ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ መከላከል ተችሏል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ጫናዎችን እንዲሁ የውስጥ አንድነትን በማጠናከር እና እጅ ለእጅ በመያያዝ ሀገር እንድትቀጥል መላው ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ዛሬም እስከ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ድረስ የቀጠለው ይኸው ነው፡፡

ለዚያ ነው የግድቡ ምርቃት ከተበሰረበት ዕለት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ባሉበት ተጠራርተው ድሉን ለማክበር አደባባይ የወጡት፡፡ ወትሮ አሻራቸውን ያሳረፉ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ደስታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በስፖርት መድረኮች በዓለም አደባባዮች ከፍ ብሎ እንደተውለበለበ ሁሉ በሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ብስራትም በሀገር ውስጥና በውጭ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ታይቷል፡፡

ዛሬ የአባይ ልጆች ተሰባስበው ለልማት በመጠራራት ድል የነሱበትን ደስታቸውን በይፋ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት መቻል መሆኑንም አሳይተዋል፡፡

እርግጥም ኢትዮጵያ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች፡፡ በአባይ ለዘመናት ስታልመው የነበረውን ብርሃን ከማግኘቷም በላይ የምጣኔ ሃብቷን አሁን ካለበት ከፍ ልታደርግ ብልጽግናውን ተያይዛለች፡፡

ከወዲያ ደግሞ ከተሞቿን በማዘመን፣ የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ፣ ኢንደስትሪውን በማበልጸግ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ከድህነት እየተላቀቀች አዲስ የብልጽግና ታሪክ እየጻፈች ስለመሆኗ በተግባር እያሳየች ትገኛለች፡፡

ታዲያ ይህ ሁሉ ሲታሰብ “ታሪክ ራሱን ደገመ” አያስብልም? ጥንት የነበረው የኢትዮጵያ ሥልጣኔና ጀግንነት ዛሬ በሕዳሴ ግድብ እና በሌሎች የልማት ሥራዎች ተመልሷልና፡፡