“ለሀገሬ ተቆርቋሪ ነኝ” – አምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ
በአብርሃም ማጋ
የዛሬው ባለታሪካችን አምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ “ለሃገሬ መዋደቄ እጅግ በጣም ያኮራኛል” በማለት ነው ከታሪካቸው መግቢያ ያካፈሉን፡፡
በዘመነ ደርግ ጊዜ ሃገራቸውን ለመበታተን ቆርጦ የተነሳው የሻቢያ ድርጊት እጅግ አስቆጥቶአቸው ነበር በገዛ ፈቃዳቸው ውትድርና ገብተው ዳር ድንበሩዋን ለማስከበር ቆርጠው የተነሱት፡፡
እንዳለሙትም ተሳክቶላቸው የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ከአዋሽ አርባ ግምባር ጀምረው በተለያዩ የአሥመራና ሌሎች የኤርትራ ግምባሮች በቆራጥነት ተነሳስተው የደም ካሣ ከፍለው ከፍተኛ ተጋድሏቸውንና ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
ለመግቢያነት ይህንን ካልን ዘንድ ከሀገር ጋር የተቆራኘውን ታሪካቸውን ልናስነብባችሁ ወደድን፤ መልካም ንባብ፡፡
አምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ በቀድሞው መንግስታዊ አወቃቀር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ በአደአ አውራጃ፣ በደብረ ዘይት ከተማ አካባቢ በ1955 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ አሁን 63ኛ እድሜያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡
የልጅነት ህይወታቸውን ያሳለፉት እንደማንኛውም አርሶ አደር ልጅ ሲሆን እስከ 12 ዓመት ድረስ ከብቶች እያገዱ፣ ለእናታቸው ከዱር እንጨት ሰብሮ በማምጣትና ውሃ በመቅዳት ማደጋቸውን ይገልፃሉ፡፡
እድሜአቸው 12 ዓመት ሲሞላቸው ከታ ተብሎ በሚጠራው በመንግስት ት/ቤት ገብተው እስከ 5ኛ ክፍል ተምረው ሳይጨርሱ ያቋርጣሉ፡፡
ትምህርታቸውን ያቋረጡት የእናታቸው እህት የሆኑት አክስታቸው ወደ ሃዋሣ ከተማ ይዘዋቸው በመምጣታቸው ነበር፡፡ ሃዋሣ ከተማ ከመጡ በኋላም ፍላደልፊያ ተብሎ በሚጠራው በሚስዮን ትምህርት ቤት አስገብተዋቸዋል፡፡
ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በዚያ ተምረዋል፡፡ በ1970 ዓ.ም ላይ የ7ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ የሻቢያና የሶማሊያ ሽፍቶች ሃገራችን ላይ ወረራ እንዳደረጉ በዜና ይሰማሉ፡፡ በወጣትነት ጊዜያቸው ወኔያቸው ተቀሰቀሰ፡፡ በወቅቱ በአክስታቸው ቤት የተትረፈረፈ ነገር ቢኖርም መከላከያ ገብተው የሃገራቸውን ድንበር ለማስከበር ቆርጠው ይነሳሉ፡፡
በተለይም በወቅቱ በሬዲዮ የሚለቀቀውን “ሆ ብሎ ሄዶ ቆርጦ ተነሳ፣ ሃገሩን ሊያስከብር አንበሳው እያገሳ” የሚለውን ዜማ ሲሰሙ በከፍተኛ ወኔ ተሞልተው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ለመሆን በቆራጥነት ወስነው ይነሳሉ።
በመሆኑም በውትድርና ተመልምለው የአዋሽ አርባ ማሰልጠኛ ገብተው የ6 ወር ሙሉ የውትድርና ስልጠና ወሰዱ፡፡
ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ በሐረር ውስጥ የረር ግንባር ይሰለፋሉ፡፡ በወቅቱ ይህ አካባቢ በሶማሊያ ሽፍቶች ቁጥጥር ስር ስለነበር ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በመፋለም ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሽፍቶቹን ደምስሰው አካባቢውን ነፃ ያወጣሉ፡፡
ከዚያም ወደ ማሰልጠኛው አዋሽ አርባ ይመለሳሉ፡፡ ተመልሰውም በማሰልጠኛው ለሳምንታት ሳይቆዩ በድንገት ሌላ ትእዛዝ መጣባቸው፡፡ በዚህ ትእዛዝ መሠረት በአፋር በመላካሳድ፣ በሚሌ እና ጐዋኔ አድርገው በአሰብ መንገድ ወደ ግራ ታጥፈው ወደ ወሎ ገቡ፡፡
ከዚያም በአላማጣ አድርገው ማይጨው ገብተው ውጊያ ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ውጊያውን በጀመሩት ከወያኔ አርነት ትግራይ ግምር ጋር ነበር፡፡ በ26ኛ መካናይዝድ ብርጌድ ውስጥ ሆነው ነበር የተዋጉት፡፡
በዚሁም ብዙ ጊዜ ሳይፈጅባቸው አካባቢውን ከወንበዴዎች እጅ ነፃ ያደርጋሉ፡፡ ውጊያው ጋብ ሲል የማጠናከሪያ ስልጠና እየወሰዱ እያሉ የሃገሪቷ መሪ ጓድ መንግስቱ ሃይለማሪያም ጦሩን ሊጐበኙና ማበረታቻ ሊሰጡ ወደ ግምባሩ ይመጣሉ፡፡ እንደመጡም ወታደሮቹን ሲመለከቷቸው ይደነግጣሉ፡፡
ድንጋጤያቸውም ሌላ ሳይሆን ወታደሮቹ በሙሉ የተቦጫጨቀ የደንብ ልብስ ለብሰው ማየታቸው ነበር፡፡ በዚሁም የጦሩን አዛዥ ጠርተው ጉዳዩን ይጠይቋቸዋል፡፡ ስለጉዳዩ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ምላሽ አለመገኘቱን ያብራራል።
በዚሁም ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ልብስ ይመጣላችኋል ብለው ቃል ገብተው ከሄዱ በ5ኛ ቀን ውስጥ ልብስ ተጭኖላቸው ይመጣል፡፡
በውትድርና ዓለም ውስጥ የደንብ ልብስ መኖር ልዩ ሞገስና ክብር እንደሚያሰጥ አምሳ አለቃው ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
በወቅቱ በውጊያው ጀብዱ ሠርተው ከመንግስቱ እጅ የማበረታቻ ሽልማት ሜዳሊያ ከተሸለሙት ውስጥ አምሳ አለቃ ታደሰም አንዱ ነበሩ፡፡
ከዚያ በኋላ በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊትን በሶስት ብርጌድ ይከፋፈላል፡፡ ብርጌድ አንድ፣ ብርጌድ ሁለትና ሶስት ተብሎ፡፡
በመሆኑም አምሳ አለቃ እጣ ተጥሎ ብርጌድ ሶስት ደረሳቸው፡፡ ከዚያም ሶስቱ ብርጌዶች በአንድ ጊዜ አሥመራ ገብተው እንዲዋጉ ትእዛዝ ተላለፈ ከአዛዦቹ፡፡ በዚሁም ተግባራዊ ተደርጐ በአንድ ቀን ውስጥ 3ቱም በየፊናቸው ተሰልፈው ከተማዋን ከሻቢያ እጅ ነፃ አደረጓት፡፡
በወቅቱ በውጊያው ውስጥ ከግምባር ቀድሞ ተዋጊዎች አምሳ አለቃ ታደሰ አንዱ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የነአምሳ አለቃ ብርጌድ በኤርትራ አድቋላ ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ መንደፈራ ገብቶ ጠላትን ድል አደረገ፡፡ በተጨማሪም አራዛ ወደሚባለው በረሃ ገብተው ጠላትን ማሳደድ ጀመሩ፡፡ ከዚያ በኋላም ሰራዊቱ ወደ ኋላ እንዲመለስ በተሰጠው ትእዛዝ መንደፈራ ተመልሰው አሥመራ ሄደው እንዲዋጉ ተደረጉ፡፡
ድሉንም ተቀዳጁ፡፡ ለአንድ ወር ያህል የአሥመራን አካባቢ ካረጋጉ በኋላ አፋቤትንና ከረንን ነፃ እንዲያወጡ ታዘዙ፡፡ በትእዛዙ መሠረት አካባቢውን ከሻቢያ ጦር ቁጥጥር ነፃ አወጡ፡፡ በቁጥጥራቸው ሥር አደረጉት፡፡
ከዚያም ለጥቂት ቀናት እረፍት ካደረጉ በኋላ ከርከብትና ሞሎክሰ ግምባር ተመድበው ነፃ አውጥተው በቀይ ባህር ዳር አድርገው አልጌና ገቡ፡፡ በአልጌናም ለጥቂት ቀናት ካካሄዱ በኋላ ወደ ኋላ እንዲመለሱ ትእዛዝ ተሰጣቸው፡፡ ከዚያም ፊታቸውን አዙረው ወደ በሸቃ ግምባር ተመድበው ከፍተኛ ጦርነት አካሂደው በጥቂት ቀናት ውስጥ አካባቢዋን ተቆጣጥረዋል፡፡
በወቅቱ ከነሱ ጋር የነበሩት 16ኛ ስንጥቅ መካናይዝድና 5ኛ አየር ወለድ ብርጌድ ነበር። ከዚያም ደቀማር ተመድበው ከሻቢያ ጦር ጋር ከፍተኛ የጨበጣ ጦርነት አድርገዋል። በወቅቱ የሻቢያ ጦር አይሎ ስለነበር ሊበገርላቸው አልቻለም፡፡
ምክንያቱም የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች በወቅቱ ከሃገር ይልቅ የግል ፍላጐታቸውን ለማሟላት ሲሉ በፈጠሩት ልልነት ነበር የሻቢያ ጦር የበላይነቱን ያሳየው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች በገንዘብ ተደልለው ሰራዊቱን ለጠላት አሳልፈው በመስጠታቸው የኢትዮጵያ ጦር ሊደክም ችሏል፡፡
በዚሁም የነአምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ ጦር መሳሪያውን እንደታጠቀ እየተዋጋም ወደ ሱዳን ለመውጣት ተገድዷል፡፡ በመሆኑም ጦሩ የያየዘውን መሣሪያ ለሱዳን መንግስት አስረክቦ በስደት በሱዳን መኖር ጀመረ፡፡ ጊዜው 1983 ዓ.ም ሲሆን የኢህአዴግና የሻቢያ ጦር ሃገሪቷን የተቆጣጠረበት መሆኑ ነው፡፡
እነ አምሳ አለቃ ታደሰ በሱዳን ለ6 ወራት ያህል ከቆዩ በኋላ ወደ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ እንደመጡም የተሃድሶ ገንዘብ ብሎ ሃገሪቷን የተቆጣጠረው የኢህአዴግ መንግስት የሁለት ወር ገንዘብ 70 ብር ለእያንዳንዱ አባል መስጠቱን ይናገራሉ፡፡ የአንድ ወር 35 ብር ለእያንዳንዱ አባል ሰጥቷል፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ገንዘቡ መቆሙን ይገልፃሉ፡፡
ከዚህ በመቀጠልም ለተወሰኑ ወራት ስንዴና ዘይት ይሰጣቸው እንደነበርም አምሳ አለቃው ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ ሆኖም እሱም ዘላቂ ሳይሆን ቀርቶ ተቋረጠ፡፡
ከዚያም አምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ አቋርጠው የሄዱትን ትምህርታቸውን መማር ጀምረው 9ኛ ክፍል አጠናቀቁ፡፡ ከሶስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በቀድሞ ደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ተወዳድረው በማለፍ በፎቶ ኮፒ ባለሙያነት ተቀጠሩ፡፡
በፍትህ ቢሮም ለ22 ዓመታት ያህል አገልግለው በጡረታ ተገለሉ፡፡ በመከላከያ ውስጥ ለ14 ዓመታት በአጠቃላይ ለ36 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡
ጡረታ ከወጡ በኋላም ሰለስታ ተብላ በምትጠራው አፀደ ህፃናት ት/ቤት ውስጥ በጥበቃ ሥራ ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ እኛም አግኝተናቸው ያነጋገርናቸው በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሥራ ላይ እያሉ ነበር፡፡
በውትድርና ጊዜ ያጋጠሟቸው ችግሮች ምን እንደሆኑም አነጋግረናቸው ነበር፡፡ የሰጡን ምላሽ ቢኖር፡-
በአሥመራ ውስጥ ወደ ምፅዋ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው ንፋሳት ተብሎ በሚጠራው ግምባር እየተዋጉ እያሉ ግራ እግራቸው ከጠላት በተወረወረ ቦምብ ተመቶ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
በመሆኑም በገጅራት ሆስፒታል ታክመው ወጥተው እንደገና ከሠራዊቱ ጐን ተሰልፈዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አካባቢው በረሃማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የምግብና የውሃ እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡
በተለይም ከረከበት፣ አልገናና በበሸቃ ግምባር እያሉ ከፍተኛ ኮሾሮና የውሃ እጥረት አጋጥሟቸው ለተወሰኑ ቀናት ያለምግብና ውሃ ማሳለፋቸውን ገልፀውልናል፡፡
ከተጠቀሰው ውጭ አካባቢው በረሃማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በእግር መዳፋቸው በግራና በቀኝ ኪንታሮት ወጥቶባቸው በሻለቃ አዛዥ ትእዛዝ ቀዶ ጥገና እንዲያደርጉ ተደርገዋል፡፡
ሆኖም በሽታው እንደገና እየተከሰተ አሰቃይቷቸው በተደጋጋሚ ቀዶ ጥገና እንደተደረጉ ሳይገልፁ አላለፉም፡፡ በዚህን ወቅት ከፍተኛ ህመምና ስቃይ እንዳጋጠማቸው ይገልፃሉ፡፡
ለሥራ ያላቸው ፍቅር ምን እንደሆነም ጠይቀናቸው ነበር፡፡ የሰጡን ምላሽ ቢኖር፡- “ለሥራዬ ትጉህ ነኝ” በማለት ነበር፡፡ በወታደር ቤት እያሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሚጣጣሩና ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ያላቸው አርበኛ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
በሥራ ቦታቸው ታማኝ፣ ሥራንና ሰው አክባሪ ናቸው፡፡ በተለይም “ለሃገሬ ተቆርቋሪ ነኝ” ሲሉ የተደመጠው ሃገራቸውን ከጠላት እጅ ለማዳን ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉት ሥራቸውንና ሃገራቸውን እንደሚያስቀድሙ በመግለፅ ነው፡፡ አክለውም ለሃገራቸው መዋደቅ ፅድቅ መሆኑን ተገንዝበው በጦሩ ውስጥ የብዙዎቹን አእምሮ አሳምነው መመለሳቸውን ያብራራሉ፡፡
በሥራ ላይ የሚጠሉት ነገር ቢኖር ጭቅጭቅና ንተርክ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በ1992 ዓ.ም ወደ ትዳር ዓለም የገቡ ሲሆን የአንዲት ሴት ልጅ አባት ናቸው፡፡ ልጃቸውም የ1ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነች፡፡
More Stories
የዓለም ሻምፒዮናን ያስወደዱ አትሌቶቻችን
“የሰው ፍቅር ስላለኝ የደረሰብኝን እንደ ጉዳት አልቆጥረውም” – አቶ ጥላሁን ጋዳና
“የግብጽ እጆች ከታሰሩ የሱዳን ተሰብረዋል”