የዓለም ሻምፒዮናን ያስወደዱ አትሌቶቻችን
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሎምፒክ በመቀጠል የዓለም ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበትና በስፖርቱ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ውድድር ነው፡፡ በሻምፒዮናው መድረክ በርካታ ስመ ጥር አትሌቶች መድረኩን ያደመቁ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ የምስራቅ አፍሪካ፣ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ለዓመታት የዘለቀ ፉክክር ውድድሩ እንዲናፈቅ ብቻም ሳይሆን የማይረሳ ትዝታን ጥሎ እንዲያልፍ ምክንያት ሆነዋል፡፡
በአጠቃላይ በተለያዩ የውድድር ዓይነቶችና በተለያዩ የውድድር መድረኮች ለአስራ አራት ዓመታት የዘለቀው ሀይሌ ገ/ስላሴ እና የፖል ቴርጋት ተቀናቃኝነት በዋንኛነት የሚነሳ ሆኖ፣ ሌሎች አትሌቶችም እንዲሁ ብርቱ ፉክክር አድርገዋል፡፡
ስፖርቱ በብዙ መልኩ በሚካሔድበት በዚህ ዘመን እንኳ እንደሀይሌ እና ፖል ቴርጋት በአስደናቂ ፉክክር ለብዙ ዓመታት የዘለቁ አትሌቶችን ለማግኘት ይቸግራል፡፡ በተለይም የሁለቱ አትሌቶች የ10ሺህ ሜትር ፉክክር በስፖርቱ አድናቂያን ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ሆኖ አልፏል፡፡
ይህን አስመልክቶ ሀይሌ ገ/ ስላሴ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡-
“ኬንያዊያንን እፈልጋቸዋለሁ፡፡ እነሱ ራስ ምታቴ ናቸው፡፡ እና ደግሞ ጥንካሬዬም ጭምር፡፡” ሀይሌ ንግግሩን ሲቀጥልም እንዲህ አለ፡-
“ያለእነርሱ እኔ ታላቅ አትሌት አልሆንም ነበር፡፡”
በሁለቱ ሀገራት አትሌቶች መካከል የሚደረገውን ፉክክር “ሠላማዊ ጦርነት” በማለት የገለጸው አትሌቱ፣ ለፖል ቴርጋትም ተገቢውን አድናቆት ቸሮታል፡-
“ሁሉም ሰው እኔ ቴርጋትን በኦሎምፒክ እንዳሸነፍኩት ይናገራል፤ ነገር ግን እርሱ እኔን በዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ስለማሸነፉ አያወራም” በማለት፡፡
ይህ የሀይሌ አባባል አትሌቶቹ በሩጫ ሜዳ ላይ ሜዳሊያ ለመነጣጠቅ ምን ያህል እንደሚጥሩ ከማሳየት በዘለለ፣ ከሜዳ ውጪ ጥሩ ወዳጅነት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው፡፡
ወደ ዓለም ሻምፒናው ስንመለስ፣ በተለይም በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች አስደናቂ ፉክክር እንደኦሎምፒኩ ሁሉ በዚህም ውድድር ተስተውሏል፡፡ ከዚህ አንጻር፣ በውድድሩ ለሀገሩ 4 የወርቅ፣ 1 የብር እና 1 የነሀስ ሜዳሊያ ያስገኘውን ሀይሌን እና የእርሱን ዘመን ብንመለከት እንኳ፣ ከቴርጋት ጋር የነበረውን ፉክክርና ሌሎች አስደናቂ ገጠመኞችን እንመለከታለን፡፡
እ.አ.አ በ1993 በጀርመኗ ስቱትጋርት ከተማ በተካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ውድድር፣ የ1991 የውድድሩ አሸናፊ ኬንያዊው ቱኖይ እና ሀይሌ ገ/ስላሴን የመጨረሻ ዙር ድራማዊ ክስተት እናስታውሳለን፡፡
ውድድሩ ሊጠናቀቅ አንድ ዙር ሲቀረው፣ ቱኖይ የአንድ እግሩን ጫማ አሽቀንጥሮ በመወርወር ፍጥነቱን ጨምሮ አፈተለከ፡፡ እግር በእግር ሲከተለው የነበረው ሀይሌ ገ/ስላሴ ፍጥነቱን ቢጨምርም፣ ኬንዊው አትሌት ግን የሚደረስበት አይመስልም ነበር፡፡ ደወሉ ከተደወለ በኋላ ሀይሌን በስድስት ሜትሮች ርቀት እየመራ ወደፊት ገሰገሰ። ውድድሩ ሊጠናቀቅ 16 ሜትሮች ሲቀሩት፣ ሀይሌ ከቱኖይ በአራት ሜትር ይርቅ ነበር፡፡ ያም ሆኖ፤ ፍጻሜው ላይ የማይበገረውና የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ደጋግሞ ያስጠራው አትሌት ከፊት ተገኘ፡፡
በቀጣዩ ዓመት ተመሳሳዩ ውድድር የኦሎምፒክ ሻምፒዮናውን ሞሮኳዊውን ሳላ ሂሱን እና የዓለም ሀገር አቋራጭ አሸናፊውን ኬንያዊውን ፖልቴርጋት ከሀይሌ ጋር አገናኘ፡፡ ከብርቱ ፉክክር በኋላ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀረው ያፈተለከው ሀይሌም ድሉን አስጠበቀ፡፡
በቀጣዩ ዓመትም በሁለቱ አትሌቶች ላይ የበላይነቱን የወሰደው ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ ለ3ኛ ጊዜ በተከታታይ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን በቃ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ሀይሌ ለ4ኛ ጊዜ አሸናፊ ሲሆን ከኋላ ቀድሞት ያለፈው ኬንያዊ አትሌት በንዴት ሲመታው የተመለከትንበት ሆኗል፡፡
በዓለም ሻምፒዮና የሀይሌን የሩጫ ዘመን መሰረት በማድረግ እነዚህን ነጥቦች ያነሳሁት፣ አትሌቶቻችን በውድድሩ መድረክ የነበራቸውን ጽናትና ብቃት ለማሳየት ያህል ነው፡፡
በዚህ ውድድር ከሀይሌ ገብረ ስላሴ በመቀጠል የመጣው ዝነኛው አትሌት ቀነኒሳ በቀለም ቢሆን በውድድሩ አንጸባራቂ ድሎችን በመቀዳጀት ዓለም አቀፍ አድናቆትን ለማትረፍ ችሏል፡፡ አትሌቱ ከ2003 እስከ 2009 በተከታታይ በ10 ሺህ ሜትር ያገኛቸውን 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ2009ኙ የበርሊኑ ውድድር በ5 ሺህ ጭምር ወርቅ በማግኘት የድርብ ድል ባለቤት መሆኑ ይታወሳል፡፡
ቀነኒሳ የድርብ ድል ባለቤት በሆነበት በ5 ሺህ ውድድር ከኬንያዊው በርናንድ ላጋት ጋር ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅም ዓለም የማይዘነጋው ሆኖ አልፏል፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ በውድድሮቹ እንደሀይሌ ጊዜ ሁሉ የምስራቅ አፍሪካ፣ በተለይም ደግሞ የኬንያ አትሌቶች ተፎካካሪዎቹ ቢሆኑም፣ በ2003 የፓሪሱ ውድድር ሀይሌን በማስከተል የድል ጉዞውን አንድ ብሎ የጀመረው ብርቱው አትሌት ግን፣ በተከታታይ ባገኛቸው 5 የወርቅ እና 1 የነሀስ በአጠቃላይ 6 ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ በማምጣት ተተኪነቱን በሚገባ አሳይቷል፡፡
ወደሴቶቹም ስንመጣ የምናገኘው ተመሳሳዩን ነገር ነው፡፡ ወደእነ ደራርቱ ዘመን ስንሔድ ዓለም የተደነቀበትን አንድ ክስተት እናገኛለን፤ እ.ኤ.አ በ2001 በኤድመንተን የተካሄደውን ውድድር። በዚህ ውድድር ዝነኛዋን እንግሊዛዊት አትሌት ፓውላ ራድክሊፍን ከኋላ ያስከተሉት አትሌቶቻችን (ደራርቱ፣ ብርሀኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚ) ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ዓለምን አስደምመዋል፡፡
ይኸው ገድል በውድድሩ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተደገመው ደግሞ በጥሩነሽ ዲባባ ዘመን ነበር፡፡ በ2005ቱ የሄልሲንኪ ሻምፒዮና፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሀኔ አደሬ እና እጅጋየሁ ዲባባ ተከታትለው በመግባት የ “አረንጓዴው ጎርፍን” ስያሜ ዳግም በደማቁ ማጻፍ ችለዋል፡፡
በፓሪስ፣ ሄልሲንኪ፣ ኦሳካ እና ሞስኮ በወርቅ ደምቃ የታየችው ጥሩነሽ ዲባባ፣ በፊንላንዷ ሄልሲንኪ ድርብ ድል ያስመዘገበችበትን (በ5 እና 10 ሺህ ሜትር ወርቅ በማምጣት) ጨምሮ 5 የወርቅ እና 1 የነሀስ፣ በድምሩ በዚህ የውድድር መድረክ 6 ሜዳሊያዎችን ለሀገሯ አስገኝታለች፡፡
ይህም በአትሌቷ ብርቱ ጥረትና ድንቅ ብቃት የተገኘ ውጤት መሆኑን ልብ ይሏል፤ ምክንያቱም እሷም በዘመኗ ስመ ጥር ከሆኑ አትሌቶች ጋር ተወዳድራ በማሸነፍ ያገኘችው ነውና፡፡ የድርብ ድል ባለቤት ከሆነችበት የበርሊኑ ውድድር ባሻገር፤ ገና በ18 ዓመት እድሜዋ የተካፈለችበትንና የመጀመሪያውን ወርቅ ያገኘችበትን የፓሪሱን ሻምፒዮና ጨምሮ፣ ህመሟን ተቋቁማ ያሸነፈችበትን የኦሳካውን ውድደር ብንጠቅስ እንኳ የአትሌቷን ጽናት መገንዘብ እንችላለን፡፡
ከዚሁ ጋር የመሰረት ደፋርን የኦሳካ የ5 ሺህ ሜትር ድል አስታውሰን ስንቀጥል፣ ከሁለት ዓመት በኋላ በበርሊኑ ሻምፒዮና የተመለከትነው ነገር የተገላቢጦሽ ነበር፤ ኬንያዊያኑ ከፊት ትመራ የነበረችውን መሰረት ደፋርን በጠባብ ልዩነት በመቅደም ወርቅና ብሩን የወሰዱበት፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በዴጉ በተካሔደው ውድድር በ10ሺህ ሜትር ኬንያዊያኑ አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት የበላይነታቸውን ያሳዩበት ውድድር ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኛ እንደማስጠንቀቂያ ደወል የሚቆጠር ነበር፡፡
በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና ግን ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር ኬንያውያኑን አስከትለው በመግባት ወርቁን ለመንጠቅ በመቻላቸው ድሉ በሴቶቹ በሁለቱም ርቀቶች ለኢትዮጵያ ሆነ፡፡ በኦሪገን ደግሞ ቤትሪክ ቺቤትን ያሸነፈችው ጉዳፍ ጸጋዬ በ10 ሺህ ሜትር፣ ሄለን ኦቡሪን ያሸነፈችው ለተሰንበት ግደይ በ5 ሺህ ሜትር በቀዳሚነት ፈጽመው ኢትዮጵያን ለድል አበቁ፡፡
ያም ሆኖ በወንዶቹ ኢትዮጵያ የበላይነት እየተወሰደባት የመጣ መሆኑ የታየበትም ሆኗል። ለዚህም እንደማሳያ ለመጥቀስ፣ በዴጉ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በ10 ሺህ ሜትር ሞፋራን አሸንፎ ወርቁን የነጠቀ ድንቅ አትሌት (ኢብራሂም ጄይላን) ለዓለም ብታስተዋውቅም፣ በ5 ሺህ ሜትር ግን ድል አልቀናንም ነበር፡፡ በሞስኮ ውድድር ደግሞ ሞፋራ በሁለቱም ርቀቶች ያሸነፈበትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚህ መልኩ ቀጥለን የ2023ቱን የቡዳፔስቱን ውድድር ስንመለከትም ነገሩ እየከፋ መምጣቱን የሚያስገነዝበን ሆኖ እናገኘዋለን፤ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ካገኘነው አንጸባራቂ ድል (ጉዳፍ ጸጋይ፣ ለተሰንበት ግደይ እና እጅጋየሁ ታዬ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከወጡበት) ውጪ በወንዶቹ በሁለቱም ርቀቶች እና በሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ውድድሮች ወርቁን በመነጠቃችን፡፡
እንደማሳያ በሁለቱም ጾታ በተለይም በሁለቱ የውድድር ዓይነቶች ላይ (5 እና 10 ሺህ ሜትርን መሰረት በማድረግ) ያደረኩት መጠነኛ ቅኝት የሚያሳየውም አሁን አሁን በአትሌቲክስ ስፖርት የሀገራችን ውጤት እየተዳከመ መሆኑን ነው። ይህም በዘንድሮው የቶኪዮ ውድድርም የታየ ክስተት በመሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡትና ሁነኛ መፍትሔ ሊፈልጉለት ይገባል፡፡

More Stories
ማርቲን ኦዴጋርድ ወደ ልምምድ ተመለሰ
ወላይታ ድቻ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አሳካ
3ኛ የመቀስ ምት ጎሉ