“የሰው ፍቅር ስላለኝ የደረሰብኝን እንደ ጉዳት አልቆጥረውም” – አቶ ጥላሁን ጋዳና
በሙናጃ ጃቢር
አካል ጉዳተኝነት በፈጣሪ ቁጣ፣ በሀጢአት ወይም ፈቅደን የምናመጣው አይደለም፡፡ ዘር፣ ቀለም እና ሀይማኖት ሳይለይ በማንኛውም ሰው እና በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለማችን ከሚገኙ ህዝቦች 15 ከመቶ በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሆኑና በተለይ ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገሮች ቁጥሩ ሊያሻቀብ እንደሚችል ይታመናል፡፡
ታድያ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ትኩረት ይሻሉ፡፡ ትኩረት ካገኙ ከራሳቸው አልፈው ለሀገር መጥቀም ይችላሉ፡፡ የዛሬ የችያለሁ አምድ ችሎ ማሳያችን በማህበረሰቡ ተገቢውን ትኩረት ስላገኙ ከራሳቸው አልፈው ህዝቡን ለመጥቀም የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ይገኛሉ፡፡
አቶ ጥላሁን ጋዳና ገጊ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በሌ ዘንበራ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡
የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በጦርነት ምክንያት ሲሆን በ1979 ዓ.ም በደርግ ዘመነ መንግስት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅለው ሶስተኛ አብዮታዊ ሠራዊት ውስጥ ነበሩ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን መራቤቴ ግንባር ላይ ሲዋጉ በጠላት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ቀኝ እጃቸው እና ግራ እግራቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው አጫውተውናል፡፡
“ወደ ጦርነት ሲገባ መሞትም ከሆነ እሞታለሁ፤ ለሀገሬ ስል ዋጋ እከፍላለሁ፤ ተብሎ በቁርጠኝነት ወኔ ተላብሶ የሚገባ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሲኖር በአንድም በሌላም ግጭት የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡
“ለሀገር ክበር ስል አካሌን በማጣቴ ምንም ተሰምቶኝ አያውቅም” ያሉት አቶ ጥላሁን፣ የማህበረሰቡ ሞራል ብርታት ስለሰጣቸው ለረጅም ዓመታት ያቋረጡትን ትምህርታቸውን እንደገና በመጀመር ለመማር ችለዋል፡፡
ወደ ግንባር ሳይሄዱ በፊት ትምህርታቸውን ሆዶ ቡልቱማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ተምረው ነበር፡፡ ከግንባር መልስ ደግሞ 8ኛ ክፍል በጀቾመ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ከ9ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በሆዶ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡
ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ውጤት ስላልመጣላቸው ወደ ኋላ ተመልሰው በ10ኛ ክፍል የማትሪክ ውጤት በዲፕሎማ መርሀ ግብር ሻሸመኔ ሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በሰው ሀብት አስተዳደር ትምህርት ክፍል እየተከታተሉ ሲሆን፥ ዘንድሮ ተመራቂ ተማሪ መሆናቸውን ገልጸውልናል፡፡
አቶ ጥላሁን ባለትዳር እና የ8 ልጆች አባት ሲሆኑ አካል ጉዳታቸው ሳይገድባቸው የቀበሌ ሊቀመንበር፣ አርሶ አደር እና የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማህበር ህብረት ሰብሳቢ ሆነው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ህብረተሰቡን እያገለገሉና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡
“ማህበረሰቡ ለኔ ጥሩ አመለካከት አለው፡፡ ‘ለእናት ሀገሩ ሲል ነው አካሉን ያጣው’ የሚል እምነት ስላላቸው ትልቅ ክበር ይሰጡኛል፡፡ እስካሁንም ድረስ ምንም አይነት የአመለካከት ችግር አልገጠመኝም፡፡ የሰው ፍቅር ስላለኝ የደረሰብኝን ጉዳት እንደ ጉዳት አልቆጥረውም በዚህም ደስተኛ ነኝ::” ብለዋል፡፡
ግንባር ባይሆኑም በተሰማሩበት መስክ ጀግነው እየሠሩ መሆናቸውን ማህበሩ ላይ የሚሰሯቸው ስራዎች ትልቅ ማሳያ ናቸው፡፡
ከሁሉም የጉዳት አይነቶች የተወጣጡ አካል ጉዳተኞች በማህበር ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በዘንድሮ ዓመትም የማህበሩን አባላት በኢኮኖሚ ለመደገፍ ፍየል ገዝተው ለ27 አካል ጉዳተኞች ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል፡፡
ከአርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል ጋር በመቀናጀት ሰው ሰራሽ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ አድርገዋል፡፡ 150 ጥንድ ክራንቾችን ለመጠባበቂያ ገዝተው አስቀምጠዋል፡፡ አካል ጉዳተኛ ለሆኑ ተማሪዎች የጽህፈት መሳሪያ ገዝተው ተደራሽ አድርገዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞችን አቅም ለመገንባት አባላቱን ተራ በተራ እየመለመሉ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ዙሪያ እና ከአመለካከት ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸውን አሉታዊ አመለካከት ቀድመው እንዲከላከሉ ከክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን በየጊዜው ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አስተዳደር የመሥሪያ ቦታ ሰጥቷቸው ወደ 89 ቆርቆሮ የሚደርስ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ጽ/ቤት ገንብተዋል፡፡ ጽ/ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ፣ የዕቃ ግምጃ ቤት፣ የሰብሳቢው ቢሮ እና የሠራተኛና ማህበራዊ ደጋፊ አካላት የሚሰባሰቡበት አጠቃላይ 5 ክፍል ያለው ነው፡፡ ክልሎችም በየጊዜው እየመጡ አደረጃጀቱን እንደሚገመግሙ እና እንደሚደግፏቸው ጭምር አቶ ጥላሁን ገልጸውልናል፡፡
“አካል ጉዳተኛ መሆን አለመቻል አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኛ እንደ ማንኛውም ዜጋ መማር፣ መሥራት፣ ማግባት፣ መውለድ፣ መዳር እና ማስተዳደር ይችላል፡፡ እኩል መብት አለው፡፡ ስለዚህ አካል ጉዳተኛ ልጅ ያለው ወላጅ ልጁን ከመደበቅ ይልቅ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ አለበት፡፡ መሠረተ ልማት ከተሟላላቸው ከመማርና ከመስራትወደ ኋላ የሚያደርጋቸው ነገር የለም፡፡
“በየቦታው የተቋቋሙ የአካል ጉዳተኞች ማህበር አካል ጉዳተኛ ማለት አለመቻል እንዳልሆነ እና አካል ጉዳተኝነት ከምንም እንደማያግድ እንደኛ ልዩ ወረዳ በየጊዜው ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
አቶ ጥላሁን እንደ ችግር ያነሷቸው ነጥቦች፥ “እንደኛ ልዩ ወረዳ ለአካል ጉዳተኛ ተብሎ የሚበጀት በጀት የለም። ወደ ውስጥ ዘልቀን ለመሥራት የበጀት እጥረት እያጋጠመን ነው፡፡ በየስብሰባው እናነሳለን ግን እስካሁንም ድረስ እልባት አላገኘንም፡፡
“በሀይማኖት ተቋማት፣ ባለሀብቶች፣ ዊማ በሚባል የውጭ ድርጅት እና በአባላት መዋጮ ነው ማህበሩን የምንደግፈው። በየጊዜው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ መንግስት ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሊደግፈን ይገባል፡፡
“ተምረው ሥራ አጥ የሆኑ አካል ጉዳተኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ተመርቀው ሥራ ለማግኘት ትልቅ ፈተና እየሆነባቸው ነው፡፡ ዘንድሮ ሁለት መምህራንን በብዙ ትግል ለማስቀጠር ችለናል፡፡ የአካል ጉዳተኛ ጉዳት ችላ ሊባል አይገባም፤ ትኩረት እንዲደረግበት አሳስባለሁ፡፡
“ባለቤቴን እና ልጆቼን እንዲሁም ደግሞ ህብረተሰቡን፥ ትምህርቴን እንድማር ሞራል ሆነውኛል፤ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
More Stories
“ለሀገሬ ተቆርቋሪ ነኝ” – አምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ
የዓለም ሻምፒዮናን ያስወደዱ አትሌቶቻችን
“የግብጽ እጆች ከታሰሩ የሱዳን ተሰብረዋል”