“የግብጽ እጆች ከታሰሩ የሱዳን ተሰብረዋል”
በፈረኦን ደበበ
ከህዳሴ ግድባችን ምረቃ በኋላ እንደነፈሰው አየር ባይሆንም ግብጽ ስታራምድ የነበረው ጥላቻ ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ የራሷ ወዳጆችን ሁሉ ያሰላቸ ድርጊት ነበር፡፡ ይህ በእውኑ እሷ የዛተችውን ያህል ትፈጽም ይሆን የሚለውን ጥያቄ ሁሉ ያስነሳል፡፡
አዎን ነገሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከሀገሯ ጀምሮ የዘረጋቻቸው የክፋት ሰንሰለቶችን ሀገራችን በየጊዜው እየበጣጠሰች ብትመጣም በምረቃ ማግሥትና ከዚያ ወዲህም ለመቀጠል ማሰቧ ወዳጅን ቅር፤ ጠላትን ደስ የሚያሰኝ ሆኗል፡፡
ከዚህ አንጻር የአፍሪካና አንዳንድ የዓለም መገናኛ ብዙሀን ቀርቶ የራሷ ወገን ከነበሩት አረብ ጋዜጦች ሁሉ ትችት ማስተናገዷ የሀገራችንን ሀቅ አጉልቶ ያሳያል፡፡
በዚህ ዓይነት ሰሞኑን የወጣው ዘገባ ገራሚ ገጽታ አለው፡፡ “የናይል ውኃ ጦርነት አብቅቷል”፣ “ኢትዮጵያ አሸንፋለች” በሚለው ርዕስ ከመጀመሩ ባለፈ ምክንያቶችንም አንድ በአንድ መዘርዘሩ ሀገራችንን ግርማ ሞገሷን አላብሶታል፡፡
ከግድቡ መጠናቀቅና ምረቃ በኋላ የሀገራችን ገጽታ ምን ያህል በዓለም አደባባይ እንደገነነ በሚያሳይ መልክ የተዘጋጀው ዘገባ በማጠቃለያው ላይ ሀገራችን አንግባ ከተነሳችው የጋራ የመልማት ራዕይ ሳትዛነፍ እንድትቀጥልም ጠይቋል፡፡
የሀገራችን ባላንጣ የሆኑት ሁለቱ ሀገራት ቀጣይ ምን ምን የፖሊሲ አማራጮችን መውሰድ እንደሚችሉና የሌሎች ጎረቤቶታችን ፍላጎት ሁሉ ያካተተው ረጅም ጽሁፍ ኢልፋድል ኢብራሂም በተባሉ ባለሙያ ተዘጋጅቶ አረብ ዊክሊ በተባለው ጋዜጣ የተሠራጨ ሲሆን የሱዳንና ዓረብ ፖለቲካ ተመራማሪ ናቸው፡፡
ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የነበረውን ውጣውረድ ሲያወሱ የዘመናችን ትልቁ የውኃ ውዝግብ ወይም ጦርነት በማለት የጀመሩ ሲሆን ትርክቱን ግን ጠንከር ያለና ቀላል ብለውታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ታዳጊ የሆነችው የላይኛው ተፋሰስ ሀገር ኢትዮጵያ በገነባችው ግዙፍ ግድብ የበላይነቷን ተቆጣጥራ የነበረችውን የታችኛው ተፋሰስ ሀገር ግብጽን ለመገዳደር መነሳሳቷ ተጠቃሽ ነው ብለውታል፡፡
ፍትጊያውን እንደ አብዮታዊ ለውጥ የሚመለከቱት ባለሙያው ውጥረቱም ባለፈው መስከረም ወር መግቢያ ላይ በነበረው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት መቋጫ አግኝቷል ብለዋል በዕለቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ “በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ታላቁ ስኬት” ያሉትን እያነሱ፡፡
ገሀድ በወጣው በዚህ በአዲሱ የግንኙነት ማዕቀፍ የግብጽ የዛቻ ምዕራፍ እንደተዘጋና ካሁን በኋላ ርዕሰ ዜና በመሆን የሚያጨናንቀው ደብዛው እንደሚጠፋ ጠቅሰው ለዚህም ቀደም ባለ ጊዜ ያሁኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተናገሩትን አፍራሽ ቃል አውስተዋል በጊዜው በካይሮ ትልቅ ድጋፍ እንዳገኘም በማስታወቅ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ይህ አማራጭ በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ መንገድ እንደማይቻላት ጠቅሰው ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግብጽ በአሁኑ ጊዜ የምትገኝበት ከባቢያዊ ሁኔታ ነው ብለውታል። ሀገራችንን ለማስገባት የሞከረችው ጫናና ውዥንብር መሠረት እንደሌለው ለመግለጽ ሲፈልጉም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የፍልስጤምና እሥራኤል ግጭትን ጠቅሰዋል ግብጽ በሁሉም አቅጣጫዎች እጇ እንደተያዘ በማመልከት፡፡
ደምሳሽ የሆነው የጋዛ ጦርነትና ሰሞኑን እሥራኤል በኳታር ላይ የወሰደችውን ወታደራዊ ጥቃት አንስተው ሲገልጹም በግብጽ ላይ እንደሚያነጣጥር ተናግረዋል መከራው ምጣኔ ሀብቷን፣ ዲፕሎማሲ አቅም እና ጸጥታ መዋቅሯን ሁሉ ከጥቅም ውጪ እንደሚያደርግ በማስታወቅ።
ለጋዛ ካላት ቀረቤታ፣ ብዙ ሚሊዮን ከሚቆጠሩ ስደተኞችና ሰፊ ቦታ ከሚያካልለው ኃላፊነቷ አንጻር ግብጽ በቀላሉ በደቡባዊ ማዕዘኗ ላይ ባለችው ኢትዮጵያ ላይ ጦር ማዝመት እንደማይቻላት የጠቀሱት ጸሀፊው 125 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሀገርን መድፈር እንደማትችልም ነው ያስታወቁት፡፡
የዚህ ዓይነት የስትራቴጂክ ማፈግፈግ ዝም ብሎ በአጋጣሚ ሳይሆን የተመረጠ የመንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ጭምር እንደሆነ ያመለከቱት እልፋድል በዚህ ጊዜ ሁሉ ዲፕሎማቶቿ “የአንድ ወገን የውኃ ሙሌት” አሊያም “የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ” የሚለውን ዲስኩር እየነዙ ህዳሴ ግድብን ለማጥላላት እንደሚጠቀሙበትም ነው ያመለከቱት በአሁኑ ጊዜ ከአባይ ውኃ ይልቅ ሌሎች ዘዴዎችን ለመጠቀም መገደዳቸውን እያመለከቱ፡፡
ለዚህ ሥራ ደግሞ እንደ አብነት የሚያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ሙስጠፋ ማድቦሊ በቅርቡ ያወጡትን መግለጫ ሲሆን በሚቀጥሉት 6 ዓመታት ውስጥ 10 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር ጨዋማ ውኃ ለማከም ዕቅድ ይዘዋል፡፡
በአባይ ላይ ያለውን የውኃ ጥገኝነት ለመቀነስ እስከ 100 የሚደርሱ የማጣሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ እንዳስገቡና አብዛኞቹ ከዓለም አቀፍ ኩባኒያዎች ጋር በሽርክና እንደሚሠሩ ጠቅሰው በዚህ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዳሰቡ አመልክተዋል፡፡
በእንዲህ ዓይነት መልኩ እስካሁን ሲሠራበት የነበረውና ለግብጽ የአንበሳውን የውኃ ድርሻ የሰጠው የቅኝ ግዛት ዘመን የውኃ ስምምነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚከስም ጠቁመው ቀጣይም ካይሮ የህዳሴ ግድብን ለማጣጣም እንጂ ለማፍረስ አታስብም ብለዋል በአረብ ዊክሊ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፡፡
የግብጽ እጆች የታሠሩና ካለው የእርስ በርስ ጦርነት አንጻር የሱዳንም የባሰ ሰባራ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡ ሀገሪቱ እያስተናገደች ካለው የተልዕኮ ጦርነት አንጻር ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነቷን ሁሉ እንዳጣች የጠቀሱት ባለሙያው በዚህ ምክንያት ፖርት ሱዳንን መቀመጫ ያደረገውና በወታደሩ የሚደገፈው መንግሥት ግብጽን እንደ በላይ ጠባቂ አድርጎ መያዙን አስፍረዋል፡፡
አነዚህ ሁኔታዎች ከመነሻው ተቃውሞ የሌላትን ሱዳንን ህዳሴን እንድትጠላ እንዳደረገ ጠቅሰው አልጀዚራ ይፋ ያደረገውና እ.ኤ.አ. በ2020 የወጣው ሰነድም ይህንን ያረጋግጣል ብለዋል በውኃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የገባቸውን ስምምነት በማስታወስ፡፡
ይሁን እንጂ ወዳጅ ከተባለችው ግብጽ ባለፈ ጠላት የተባለችው ኢትዮጵያ እንደረዳቻትም ነው የሚያነሱት ለሦስት ዓመታት ያህል ያልከፈለችው የ90 ሚሊዮን ዶላር ውዝፍ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ስለሚጠበቅባት፡፡
የዚህ ዓይነት የተዛባ ግንኙነት የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን ከመቀራረብ ይልቅ ወደ መለያየት ሊያመራ እንደሚችልም ነው ባለሙያው በዓረብ ዊኪሊ የገለጹት ውሎ አድሮ ግብጽን ካለ ወዳጅ ሊያስቀራት እንደሚችልም በማስታወቅ፡፡
ሌላው ለኢትዮጵያ ጥሩ ዕድል ብለው የገለጹት የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ሚና ሲሆን ይህች ሀገር ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከምትታወቅበት የሸምጋይነት ሚና ወደ ባለድርሻነት መዞሯ ሲሆን ይህም በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ከገባቸው ውል ጋር እንደሚያያዝም ጠቅሰዋል፡፡
ግብጽ ልትፈጽም ያሰበችው ድርጊት መምከኑ ቀጣይ ሀገራችን የባህር በር ለማግኘት የያዘችውን ፍላጎት ለማሳካት ሁሉ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ሲሆን ካሁን በፊት ከሶማሊ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ጠላቶቿን በማበረታታት ረገድ የተጫወተውን ሚናም አብራርተዋል፡፡
ሌሎች ማሳያዎች ብለው የጠቀሷቸው ጉዳዮች በቀጠናው ግብጽ አጋር ብላ ያስቀመጠቻቸው ሀገራት ከኢትዮጵያ መዳፍ መውጣት ያለመቻላቸው ሲሆን ይህም በተለይ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን ይመለከታል፡፡
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሴን ሼክ መሀሙድ በተመለከተ በሀገራቸው ጸጥታ ማስፈን አቅቷቸው በኢትዮጵያ ወታደሮች መታገዙን የሚያነሱት ባለሙያው አልሻባብ ሊፈጥርባቸው የሚችለውን ሥጋት በዚህ መልክ መግታታቸውንም አብራርተዋል፡፡
በህዳሴ ግድብ ምረቃ ዕለት በደስታ እየተፍለቀሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መሳሳማቸው የወዳጅነታቸው ሌላ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል በመጨረሻ ንትርኩን በአሸማጋይነት ለመያዝ ያቀረቡትን ሀሳብ ሁሉ እየጠቆሙ፡፡
ስለ ኬኒያና ደቡብ ሱዳንም ሲያነሱ በተለይ ኬኒያ አስቀድማ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደንበኛ እንደሆነችና ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በክብር እንግድነት መገኘታቸውን ጠቅሰው ደቡብ ሱዳንም ቢሆንም እስካሁን ግብጽ ስትሰጣት ከነበረው የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍና ሰብአዊ እርዳታ ሰፊ የኃይል ምንጭ ያላት ጎረቤቷ እንደምትበልጥ አሳይተዋል፡፡
በእንዲህ ዓይነት በስኬታማ መሥመር ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ወደፊት ምን ለመሥራት ታስብ ይሆን በሚል ዓይነት ባነሱት ነጥብ ላይም አደራ የሚመስል አይነት መልዕክት አስተላልፈዋል መልሱ የራሷ እንደሆነም በመጠቆም፡፡
መልሱ ለዘመናት የቆየውን ህልም ማሳካት ብቻ አለመሆኑን ተናግረው በእውኑ ግድቡን ቃል በገባችው መሠረት ለአካባቢያዊ ውህደት ትጠቀም ይሆን የሚለውን ጥያቄም አጉልቷል፡፡
ግድቡ ቢያልቅም አዲሱ የናይል ታሪክ ገና ተጀምሯል ባሉበት መልዕክት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
More Stories
“ለሀገሬ ተቆርቋሪ ነኝ” – አምሳ አለቃ ታደሰ ረጋሣ
የዓለም ሻምፒዮናን ያስወደዱ አትሌቶቻችን
“የሰው ፍቅር ስላለኝ የደረሰብኝን እንደ ጉዳት አልቆጥረውም” – አቶ ጥላሁን ጋዳና