የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ “ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት!” በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ክላስተር ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ጀምሯል

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ “ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት!” በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ክላስተር ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ጀምሯል

በስልጠናው 212 አሰልጣኝ መምህራን እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።

በቢሮው የተቋማት አግባብነትና ጥራት ባለሙያ አቶ ሽመልስ ባቲሳ፤ ስልጠናው የአሰልጣኞችን አቅም ለማሻሻል ታስቦ የዳሰሳ ጥናት የተደረገበት ነው ብለዋል።

ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የአሰልጣኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው የብቃት ክፍተታቸውን ለማስተካከል ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በቢሮው አዘጋጅነት እየተሰጠ የሚገኘዉ ስልጠና ለተከታታይ 12 ቀናት የሚቆይ መሆኑንም አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

ሰልጣኞች ስልጠናውን በትኩረት በመከታተል የሚያገኙትን አዳዲስ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አንዱዓለም ገብረመድህን፤ የስልጠናው ዓላማ አሰልጣኞች ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቁ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናውን 212 አሰልጣኝ መምህራን እንደሚወስዱ የተናገሩት ዲኑ፤ ሰልጣኞች በንቃት በመሳተፍ ውጤታማ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የካፋ ዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልዮን ኃይሌ በበኩላቸው፤ አሰልጣኞች በየጊዜው በሚደረጉ ምዘናዎች አቅማቸውን በማሻሻል ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ስልጠናው የንድፈ ሀሳብና ተግባር ተኮር መሆኑን ጠቁመው፤ ሰልጣኞች ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ሀብታሙ ኃይሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን