“የሀገር ሽማግሌዎች ለህሊናቸው የሚሰሩ እንጂ የፖለቲካ ተልዕኮ የላቸውም” – የሀገር ሽማግሌ አቶ ሰይፉ ለታ
በደረሰ አስፋው
በመምህርነት ዘመናቸው ብዙ አንቱ የተባሉ ትውልዶችን አፍርተዋል፡፡ በተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች በመምህርነትና ርዕሰ መምህርነት በማገልገል ወጣት ተማሪዎችን በስብእና አንጸው በማብቃት ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያበረከቱ ናቸው፡፡ በዚሁ ሙያ ለ24 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ተዘዋውረው ባገለገሉባቸው በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ የሀገራችን ክፍሎች አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መስርተው ለተጠቃሚዎች አበርክተዋል፡፡
በሚወዱት የመምህርነት ሙያ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ህዝብን በትጋት በማገልገላቸው ዛሬም ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ ከሚወዱት የመምህርነት ስራቸው በጡረታ ተሰናብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ “መስራት ያስከብራል” የሚል አመለካከት ያላቸው ባለታሪካችን በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው ደግሞ ህይወታቸውን ለመለወጥ ይተጋሉ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም የሀገር ጉዳይ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል፣ የኔ ነግዶ ማትረፍም፣ ወልዶ መሳምና መዳር፣ ወጥቶ የመግባት ዋስትና የሚረጋገጠው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው በሚል በሀገር ሽማግሌነት እያገለገሉ ይገኛል፡፡
የተጣላን ያስታርቃሉ፤ የተበደለን እንዲካስ ያደርጋሉ፤ አካባቢያቸው የሰላም ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ግጭት ባለበት አካባቢና መንደር ሁሉ እየተንቀሳቀሱ ግጭት፣ ጦርነት፣ ኋላ ቀርነትና ድህነት ይብቃን እያሉ ትውልዱን በመልካም ባህሪ በማነጽ ይተጋሉ። በሚፈጠሩ የስብሰባ መድረኮች ሁሉ ስለሠላም ይሰብካሉ፡፡
“ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ናት” የሚሉት ባለታሪካችን ይህን ጠቃሚ እሴት በተገቢው ብንጠቀምበት ኖሮ በሀገራችን ፈጽሞ ግጭት ሊኖር አይገባም ነበር በማለት ነው የተናገሩት፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ መሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በሀገራችን ሠላምን ለማጽናት ከምንጊዜውም በላይ ሊተጉ የሚገባበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው ሲሉም ነው ሀሳባቸው የጀመሩት፡፡
እኛም እንደ ሀገር ሽማግሌነታቸው በአሁን ወቅት በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች መንስኤውና መፍትሄው ምን ሊሆን እንደሚገባ ቆይታ አደረግን። እሳቸው በሚኖሩበት ክልል አንጻራዊ ሠላም ቢኖርም ይሄንኑ በማጽናት ረገድስ ምን ሊደረግ ይገባል? የሀገር ሽማግሌዎች ሚናስ ምን መሆን እንዳለበት ቆይታ አድርገን ልምዳቸውንና ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
አቶ ሰይፉ ለታ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በወላይታ ዞን ባይሮ ኮሻ ወረዳ ልዩ ስሙ መሰና አሁን ላይ ቡከማ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በበቅሎ ሰኞ እና ሊጋባ በየነ አባ ሰብስብ ከተማሩ በኋላ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው የተቀላቀሉት። በዚህም ለአራት ዓመታት የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቀው በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡
በተመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በመምህርነት እንዲሁም በርዕሰ መምህርነት በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሀገር የሴቲት ሁመራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ስራ ሲጀምር በመምህርነት በኋላም በርዕሰ መምህርነት ያገለገሉበት የስራ ጅማሬያቸው ነው፡፡
ከ2 ዓመታት የአገልግሎት ቆይታም በኋላ ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ወረታ ከተማ በመምጣት የወረታ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲመሰረት እሳቸውም በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት በማገልገል አሻራቸውን ያሳረፉ ባለታሪክ ናቸው፡፡
በብሄራዊ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠውን ፈተና አልፈው ወደ ደብረታቦር ከተማ ተዛውረው በደብረታቦር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርዕሰ መምህርነት በማገልገል ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ትጉህ መምህርና አስተዳደርም እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ በአካባቢው በወታደራዊ መንግስት ደርግ እና ህወሀት መካከል በነበረው ጦርነት የጸጥታ ችግሩ እየጎላ በመምጣቱ በዚህ አካባቢ ብዙም በማስተማር አልዘለቁም፡፡ ትዳር መስርተው፣ ልጅ ወልደው ቤተሰብ የመሰረቱበትን አካባቢም ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡
በዚህም ወደ ኦሮሚያ ክልል ጎባ ከተማ አዝማች ደግለሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውረው ማስተማር ጀመሩ፡፡ በሰሜኑም ሆነ በኦሮሚያ ክልል በነበራቸው የአገልግሎት ዘመን ሊዘነጉ የማይችሉ ጥሩ የቆይታ ጊዜ እንደነበራቸው ያወሳሉ። በተለይ በመምህርነት እና በኃላፊነት ያገለገሉባቸው ጊዜያት ትጋትን፣ ከህዝብ ጋር ተፈቃቅሮና ተከባብሮ መስራት፣ የነገን የሀገር ተረካቢዎችን በማሰብ ካለምንም መሰልቸትና ድካም ተማሪዎቻቸውንና ማህበረሰቡን ያገለገሉበት የትጋት ጊዜ መንፈሳዊ እርካታን እንዳጎናጸፋቸው ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ ላይ እየሰሩ በነበረበት ወቅት ነው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተዛውረው በሶዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መስራት የጀመሩት፡፡ ይሁን እንጂ በዚህም ስፍራ ረጅም የሚባል ጊዜን አላገለገሉም፡፡ ምክንያቱም በአሜሪካ ከነበሩ ቤተሰቦቻቸው በተደረገላቸው ጥሪ ማስተማሩን አቋርጠው በመሄድ ለ19 ዓመታት በሀገረ አሜሪካ እንደቆዩ ገለጹልን። ለ19 ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው በሌላ ማህበራዊ አገልግሎት ነው የተሰማሩት፡፡
የወላይታ ማህበረሰብ በሰጣቸው ሀላፊነት የሀገር ሽማግሌ በመሆን በአካባቢውም ይሁን በሀገር ደረጃ ሠላምና ጸጥታን በማስፈኑ ሂደት ከህብረተሰቡና ከመንግስት ጋር በመሆን የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆነ አጫወቱን፡፡ በዚህም የሀገር ሽማግሌዎች ጉባኤ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአንጻራዊነት የተሻለ ሰላም እንዳለ የገለጹት ባለታሪካችን በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችም ቢሆን ማህበረሰቡ ለዘመናት ባካበተው የእርቅ ስርአት ችግሮችን እንደሚፈታ ነው የተናገሩት። “ባለህ ዕድሜ ህዝብን ማገልገል መታደል ነው” ይላሉ ባለታሪካችን አቶ ሰይፉ፡፡
አባቶቻችን በመልካም እሴት አንጸው አሳድገውናል፤ እኛም በዘመናችን ይህን ጠቃሚ እሴት ለህዝብ ጥቅም ማዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለትውልድም በሚጠቅም ነገር ተሳትፎ አሻራን ማሳረፍ ከአባቶቻችን የወረስነው ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ነው ያሉት፡፡
በስራ አጋጣሚ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉም ማህበረሰብ የሚተዳደርበት የሽምግልና ስርአት እንዳለ ተመልክተዋል፡፡ ማህበረሰቡ ለሽምግልና ስርአቱ ይገዛል፤ ይተዳደርበታል፡፡ የችግሮቹ፣ የግጭትም ቁልፍ መፍቻ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
ይህን ደግሞ በአግባቡ ከተጠቀምንበት በርካታ ጥቅሞች እንደሉት ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም የሀገር ሽማግሌዎች ከአባቶቻቸው የወረሱትን የሽምግልና ስርአት በየአካባቢው ለሚከሰት የጸጥታ ችግር ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
በወሰን ይገባኛል፣ በጎሳ ግጭትና በፖለቲካ አመለካከት የተነሳ ለተፈጠረ ቁርሾ፣ በትዳር ይሁን በሌሎች ምክንያቶች የተጣሉትን በማስታረቅ ጥሉ እንዳይሰፋና ማህበራዊ ቀውስ እንዳይከሰት ከሽማግሌዎች የሚጠበቅ እንደሆነ ገልጸው ይህ ኃላፊነት የሳቸውም እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ትናንሽ የሚመስሉ ነገር ግን በጊዜ ሂደት ፖለቲካዊ መልክን እየያዙ በመሄድ ነው ለሀገራችን የጸጥታ ችግር የሚሆነው ያሉት የሀገር ሽማግሌው አቶ ሰይፉ ለዚህም አባቶች ተግተው እንደሚያገለግሉ ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ሀገሮች በጠንካራ ባህላዊ እሴቶቿ የምትታወቅ ሀገር እንደሆነች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፤ ያደጉበትም ማህበረሰብ በዚህ ስርአት ኮትኩቶ እንዳሳደጋቸው ይገልጻሉ፡፡ የተጻፈ ህገ መንግስት ባልነበረበት ወቅት እንኳ አባቶች በጥላ ስር ተሰብስበው በባህላዊ እርቅ ስርአት ችግርን በመፍታት ሠላምን የማስፈን ልምድ አላቸው ብለዋል፡፡
ይህን የቀደሙ አባቶች አደራ በመረከብም የዛሬው የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች በየአካባቢያችን ሰላምን በማስፈን የድርሻችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቃሚ እሴታችን ተሸርሽሮ ልዩ መልክን እየያዘ መጥቶ ዛሬ ላይ ለምንገኝበት የጸጥታ ችግር ዳርጎናል ብለዋል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚፈጠረው የጸጥታ ችግር እየሰፋ በሌሎችም ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው፡፡
እኔ ደጅ ስላልደረሰ ተብሎ ዝም ከተባለ ነገ ደጅህ ላለመምጣቱ ዋስትና ስለሌለ በየአካባቢው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ መሪዎችና የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ወጣቶች የተበላሸውን በማስተካከል ለችግሩ የመፍትሄ አካል መሆን አለብን ነው ያሉት፡፡
“ሽማግሌዎች ለህሊናቸው የሚሰሩ ናቸው እንጂ የፖለቲካ ተልዕኮ የላቸውም” ያሉት አቶ ሰይፉ ህዝቡም ለዚህ ዓላማ መተባበር ይገባዋል ብለዋል፡፡ “በጸጥታ ችግር ብዙ ነገር እያጣን እንደሆነ ሁሉም ልብ ሊል ይገባል። ሀገራችን መልካም የአየር ጸባይ፣ ሰፊና ለም መሬት፣ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች ባለቤት፣ የተማረ እና ታታሪ ህዝብ ያላት ሆና ሳለ ይህን እድል መጠቀም አለመቻሏ ይቆጫል፡፡ ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎች ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡” ብለዋል፡፡
በአመጽ ኪሳራ እንጂ ማትረፍ የለም የሚሉት የሀገር ሽማግለው አቶ ሰይፉ በየአካባቢው ሠላምን ለማስፈን ወጣቱም ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የጸጥታ ችግሩ በኢትዮጵያ በዘመናት ታሪክ ያልተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም በእድሜያቸው እንደዚህ ሀገርን የሚያውክና ህልውናዋን የሚፈታተን ችግር አይተው እንደማያውቁ ነው የገለጹት፡፡
“ይህ የጸጥታ ችግር የመንግስትንም በጀት እያናጋ እንደሆነ ስለመታዘባቸው ገልጸው መንገድ በመዝጋትም ህዝቡ ተንቀሳቅሶ እንዳይሰራ እያወከ ይገኛል፡፡ ይህም የዋጋ ንረትን በመፍጠር የኑሮ ውድነቱን በማባባስ በመንግስት ላይ ጫናን ይፈጥራል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ተጎጂ የሚያደርገው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ስለሠላም መዘመር አለበት፡፡
“በኢትዮጵያ የተጀመረው የምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ማሰባሰብ ለሀገራችን ሠላም ወሳኝ ነው፡፡ በሚቀርቡ አጀንዳዎችም ህብረተሰቡ ተሳታፊ በመሆን የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችም የቀደመውን የመከባበር እሴት በትውልዱ በማስረጽ ሀገርን መታደግ አለባቸው፡፡” ሲሉም ይመክራሉ፡፡
በሚፈጠረው ግጭት በርካታ ህጻናትና ወጣቶች ከትምህርት ውጪ መሆናቸው እንደሚያሳስባቸው አንስተው የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም በገለልተኝነት በመስራት በሀገራችን ሠላምን ማምጣት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡
“ግጭቱ በውጭ ወራሪዎች የተከሰተ አይደለም፤ በሀሳብ ባለመግባባት የተፈጠረ እንጂ፡፡ ለዚህ መፍትሄው በእጃችን ስላለ የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት ይገባል፡፡ የሠላም እጦት ችግሩ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ይህን ለመቅረፍ ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል፡፡ ጦርነት ይብቃን ማለት አለብን። ችግርን መፍቻው ቁልፍ ነገር ውይይት በመሆኑ ይህን ባህል ማዳበር ያስፈልጋል፡፡
“በዓለም አቀፍ ደረጃ በህዝብ ብዛታቸው የሚታወቁት ሀገራት በኢኮኖሚያቸውም የመሪነቱን ስፍራ ይዘዋል፡፡ የህዝባቸውን ብዛትም እንደ አንድ ሀብት ተጠቅመው የመበልጸጊያ መንገድ አድርገዋል፡፡ የህዝብ መብዛት የችግር ወይም የግጭት ምክንያት አይሆንም፡፡ ሰፊ ህዝብ መሸከም የሚችል ሰፊ መሬትና በተፈጥሮ ሀብትም የታደልን ነን፡፡” ብለዋል፡፡
የልጅነት እድገታቸውን ሲያስታውሱ ለሽማግሌዎችም በመንገድ በቅሏቸውን ተቀብለው በማሳረፍ፣ የተሸከሙም ካሉ ሸክማቸውን አግዘው፣ ወንዝ ከሞላም አሻግረው፣ የመሸበትንም እግር አጥበው በማሳደር ማደጋቸውን ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡ ዛሬ ይህ አለ ወይ ሲባል የለም፡፡ ትውልዱ ታዛዥ አይደለም፡፡ ይህ እንዲህ ሆኖ መቀጠል የለበትም፤ የሀገር ሽማግሌዎች የቀደመውን እሴት ለትውልዱ በማስረጽ ትውልዱን ብሎም ሀገርን ከችግር መታደግ ይገባል፡፡” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“የህብረተሰቡ ተሳትፎ ለተመዘገበው ውጤት ድርሻው የጎላ ነው” – የሲዳማ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ
“አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል”
የአዲስ ዓመት ተስፋ