የመስቀል ደመራ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ነጻ ለማውጣት ወደ ምድር በመምጣት ተሰቅሎ ጨለማን ወደ ብርሃን የቀየረበት መሆኑን በዳውሮ ዞን የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ

የመስቀል ደመራ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ነጻ ለማውጣት ወደ ምድር በመምጣት ተሰቅሎ ጨለማን ወደ ብርሃን የቀየረበት መሆኑን በዳውሮ ዞን የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የዳውሮ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ኃይል ቆሞስ አባ ክንፈ ገብርኤል ገበየሁ፤ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ክብረ መስቀሉ ለዓለም የሚታወጅበት የቤተክርስቲያኗ ትውፊት እና ሥርዓት በይፋ የሚገለጥበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓሉ ሲከበር አንዱ ከሌላው በመደጋገፍ መሆን እንዳለበትና በቤተክርስቲያን አስተምህሮ “የተቸገረውን መግብ ላጣው አበድር” ስለሚል ሁላችንም የተቸገሩትን በማገዝ በዓሉን ማክበር እንዳለብን አሳስበዋል፡፡

ሥነ-ስርዓቱ ፍቅር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ መተሳሰብና መረዳዳት የሚገለጽበት እንዲሁም ዜጎችን የሚያቀራርብ ድንቅ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል።

መስቀል ፍቅር ነው፣ መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለአንዳች ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ህይውቱን በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን የገለጸበት በዓል በመሆኑ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተርጫ ቅዱስ ዮሴፍ ደብር አስተዳዳሪና አገልጋይ ቆሞስ አባ ላቤና ለሚ፣ የመስቀል በአልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኒቱ የ2018 ዓ.ም የመስቀል በአልን በሐይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓት በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅታለች። በአሉን አምና አክብረን ዘንድሮም በሰላም ስላደረሰን ለፈጣሪ ምስጋና የምናቀርብበት እንዲሁም የሚመጣውን ዓመት በበረከት እንዲሞላልን ጸሎታችንን የምናደርስበት ነው ብለዋል።

አባ ላቤና ለሚ አክለውም፤ “እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮት፣ የመስቀል በአል ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በአላት ሲመጡ ለነፍሳችንና ለስጋችን የሚያስፈልገውን ከማዘጋጀት ባሻገር የእምነታችንን ትውፊትና የክርስትናችንን ስም በማይቃረን መልኩ በሥርዓት መብላት፣ መጠጣትና መደሰት ይገባናል ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ለራሳችን ከምንመገበው ባሻገር ደካሞችን መርዳት እና ጉድለታቸውን በመሸፈን በአንድነት መደሰትና ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንዳለብን አገልጋይ ቆሞስ አባ ላቤና ለሚ አሳስበዋል፡፡

በተጫማሪም የመስቀል በአል አዲስ ዓመትን ተከትሎ የሚከበር በመሆኑ በአዲስ ዓመት አዲስ የምንሆንበትና እንደ ደመራ ብርሃን ሕይወታችንን በብርሃን እንድንመራና ወደፊትም በሕይወታችን እንደ ችቦ እያበራን እንድንጓዝ የሚመክር ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በመጨረሻም “ይህ የእንኳን አደረሳችሁ የደስታ መልዕክታችን በቤታችን ብቻ እንዳይቀር፣ በክርስቶስ መስቀል ያገኘነው ፍቅር ለሁሉም ቦታ እንዲደርስ፣ በተጠራንበት አገልግሎት በየእምነታችን አንድነትና ፍቅር የምንሰብክበት፣ በነፍሳችን ብቻ ሳይሆን በስጋችንም ለደካሞች የምንደርስበት፣ ሁላችንም የምንነቃበትና ደስታችንን የምናበዛበት ዓመት ይሁንልን በማለት ሁላችንንም እንኳን ለ2018 ዓ.ም የመስቀል በአል በሰላም አደረሰን!” ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ቅድስት ዐቢይ – ከዋካ ጣቢያችን