በሀዲያ ዞን የሆመቾ ከተማ አስተዳደር ከሀንዳ ኪና የበጎ አድራጎት ህብረት ጋር በመተባበር የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ለአቅመ ደካሞች የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ

በሀዲያ ዞን የሆመቾ ከተማ አስተዳደር ከሀንዳ ኪና የበጎ አድራጎት ህብረት ጋር በመተባበር የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ለአቅመ ደካሞች የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ

በህብረተሰቡ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የመደጋገፍ እና የመተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል።

በድጋፍ መርሃ ግብሩ የማገዶ እንጨት ከጀርባቸው ተሸክመው በመሸጥ ለሚተዳዳሩ ለአምስት እናቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ የጭነት አህያ እንዲሁም በግለሰብ ቤት ተቀጥረው እንጀራ ለሚጋግሩ ለአራት እናቶች ለደረቅ እንጀራ ንግድ ስራ መነሻ ከፒታል የሚሆን 50 ኪሎ ግራም ነጭ ጤፍ እና ማገዶ ቆጣቢ የእንጀራ ምጣድ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

በተጨማሪም ለሁለት ወጣት ሴቶች ለጀበና ቡና ቤት ሙሉ ዕቃ፣ መስራት እየቻለ የኢኮኖሚ አቅም ላነሰው ለአንድ ወጣት ለሊስትሮ ስራ የሚሆን ሙሉ ዕቃ ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን ለ20 ቤተሰቦች ለመስቀል በዓል ቅርጫ ስጋ የሚሆኑ ሁለት ሰንጋዎችን ድጋፍ ማድረግ ተችሏል።

የሆመቾ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ምስጋና አለሙ እና የሀንደ ኪና በጎ አድራጎት ህብረት አስተባባሪ ወጣት ፊታሞ ተስፋዬ በድጋፉ ወቅት እንደተናገሩት ሀንደኪና በጎ አድራጎት ኅብረት ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ ሀገራት በሚኖሩ በአካባቢው ተወላጅ ወጣቶች የተቋቁመ በበጎ አገልግሎት የተሰማራ ኅብረት ነው።

በሆመቾ ከተማና በአካባቢው የኢኮኖሚ አቅም ችግር ላለባቸው ከ30 በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች በ3 መቶ 23 ሺህ 2 መቶ 50 ብር ወጪ የመስቀል በዓል መዋያ ሰንጋ እና ቋሚ የገቢ ማስገኛ የሚሆኑ ድጋፎችን ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ህብረቱ ከሶስት አመታት ወዲህ በበዓላት ወቅት የማዕድ ማጋራት ድጋፎችን እያደረገ መቆየቱንም ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የመደጋገፍ እና የመተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ከንቲባው አሳስበዋል።

ያነጋገርናቸው ድጋፍ የተደረገላቸው እናቶችም በተሰማሩበት የስራ መስክ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን በመቆጠብ ኑሯቸውን የሚለውጡበት ቋሚ ድጋፍ ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

በተደረገላቸው ድጋፍ ራሳቸውን ለመለወጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን