በቡርጂ ዞን ለሚገኙ የተለያዩ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ሀዋሳ፡ መስከረም 13/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡርጂ ልማት ማህበር ከዞኑ የተለያዩ አከባቢዎች ለተወጣጡ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
በመረሃ ግብሩ የተገኙት የቡርጂ ዞን ብልፅግና ፓርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡሜ ቾኮል የትምህርት ዘርፍ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው፥ ልማት ማህበሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለሰራው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ አመስግነዋል፡፡
የቡርጂ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በርሱ ህርባዬ በበኩላቸው፥ የትምህርት ብክነት ለማስቀረት እና መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ ድጋፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፥ ትልቁ ግባችን የተደገፉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው ማየት ነው ብለዋል።
የቡርጂ ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ጩሙኦ፥ በ5 ቀናት ወስጥ ከ47 ሺህ ብር በላይ ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ 50 ለሚሆኑ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተው ለጥያቄያቸው በጎ ምላሽ የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎችንም አመስግነዋል ።
ድጋፉ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ብሌን ወየሳ እና ተማሪ ምርቃት አይላሞ በሰጡት አስተያየት የተደረገላቸው ድጋፍ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያደርግ በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን አንስተው ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ ፡ ቦጋለ ሉሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ “ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት!” በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ክላስተር ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ጀምሯል