በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ አርሶ አደሩ ማሳውን በጤፍ ሰብል በኩታ ገጠም በመሸፈን ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
በልዩ ወረዳው በምርት ዘመኑ በመኸር እርሻ ከለማው 12 ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም የጤፍ ሰብል የተሸፈነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል እንደገለፁት፤ በ2017/18 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ 12 ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት በዋና ዋና ሰብሎች በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡
በተለይም አርሶ አደሩ ለግብርና ሜካናይዜሽንና ለኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አቶ አብድልሽኩር፤ በልዩ ወረዳው በጤፍ ሰብል በዘር ከተሸፈነው 10 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 7 ሺህ ሄክታሩ ኩታ ገጠም የጤፍ ሰብል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ ዳፕና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ስራ መሰራቱን የተናገሩት አቶ አብድልሽኩር፤ አሁን ላይ የአረምና የተባይ ቁጥጥር እንዲሁም የዩሪያ ማዳበሪያ የመስጠት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የምርት ዘመኑ የዝናብና የአየር ሁኔታ ለመኸር እርሻው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለፁት ሃላፊው ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
አርሶአደሩ የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራን በአግባቡና በወቅቱ በማከናወን ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ለአርሶ አደሩ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት በወቅቱ ተደራሽ በማድርግ ምርታማነቱን ለማሳደግ በቅርበት የድጋፍና ክትትል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ አቶ አብድልሃሚድ ደሊል በልዩ ወረዳው የሱንካ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ ናቸው፡፡
በምርት ዘመኑ የመኸር እርሻ በቀበሌው 420 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በጤፍ መልማቱንም ተናገረዋል።
በልዩ ወረዳው በሌንጫ፣ በቄረምሳና በሱንካ ቀበሌዎች አግኝተን ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ሀጅ ተማም አህመድ፣ ረሻድ ኦሊ እና በይሳ ኩማ በሰጡት አስተያየት፤ በግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ በመታገዝ ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሻሻል ማሳቸውን በጤፍ ሰብል በኩታ ገጠም በዘር መሸፈናቸውንና አሁን ላይ የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ወለላ ኤልያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም
“የወል ሙዳይ” – ዘጋቢ ፊልም #ደሬቴድ፣ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም
የቀን 6፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም