ፎረሙ ከተሞች ያላቸውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም አቅም የሚያንጸባርቁበት ነው – ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ
የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከተሞች ያላቸውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም አቅም የሚያንጸባርቁበት መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለፁ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከአፋር ክልል መንግስት ጋር በመተባበር በሰመራ ሎግያ ከተማ “የከተሞች እድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሃሳብ ከህዳር 6 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ከለውጡ ወዲህ ለከተሞች በተሰጠው ትኩረት ከተሞች በከፍተኛ ደረጃ እያደጉና እየተለወጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች እና አጠቃላይ የልማት ስራዎች ለዜጎች ምቹ የመኖርያ አካባቢ መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።
የዚሁ አካል የሆነው የከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው፥ ዓላማውም በከተሞች መካከል የትብብር መንፈስን ማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ወንድማማችነትን በማጎልበት ፉክክርን ማዕከል ያደረገ የስራ ባህልን እንደሚያሳድግ ነው በመግለጫቸው ያመላከቱት።
ኢዜአ በዘገባው እንዳመላከተው፥ ፎረሙ ከተሞች ያላቸውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም አቅም የሚያንጸባርቁበት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
እንዲሁም ከተሞች በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በምግብ ዋስትና እና ሌሎች መሰል ዘርፎች ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በመርሃ ግብሩ 150 ከተሞች ተመዝግበው የሚወክሏቸውን አካላት እንደለዩና ከ10 በላይ የንግድ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በፎረሙ ኤግዚቢሽንና በተለያዩ መስኮች የተከናወኑ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን በከተማ ልማት ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በፎረሙ ከተሞች ራሳቸውን ለማሳደግ የ10 አመት ስትራቴጂክ እቅድ በመንደፍ ያከናወኑትን ተግባር በማወዳደር የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ከተሞች ሽልማት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የከተሞችን ውበትና ፅዳት ለማስጠበቅ ከተሞች እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ እንደሚፈተሽም ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም በመርሃ ግብሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ከተሞች እና የንግድ ድርጅቶች ምዝገባቸውን እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
More Stories
ምግብና ሥርዓተ-ምግብን በማሻሻል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ ገለጸ
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምርምር የተረጋገጡ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
የቀይ አፈር ሙሉ ወንጌል ነህምያ የልጆች ልማት ከደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ሕፃናት መምሪያ ጋር በመተባበር “የዎና ናና” የህፃናት ልማት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በዲመካ ከተማ ተካሂዷል