የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ በነገው ዕለት የሚካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም  እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የሀዲያ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ በነገው ዕለት የሚካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም  እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የሀዲያ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ

በተያያዘም በዞኑ በሰሞኑ የሚከበረው የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል እና የመስቀል ደመራ ስነስርዓት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።

ህብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለዞኑ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣም መምሪያው አሳስቧል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ በሀዲያ ዞን በነገው ዕለት መስከረም 10/2018 ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ይካሄዳል።

የሀዲያ ዞን ሰላምና ፀጥታ መመሪያ ኃላፊ አቶ ደመቀ በዶሬ እንደገለጹት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ መምሪያው ከሚያከናውናቸው የትኩረት መስኮች አንዱ በመሆኑ ከሚመለከታቸው ተጠሪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

ተከታታይ በሆኑ በዓላት ወቅት ለሰላም ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት በነገው ዕለት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ በሆሳዕና ከተማ የሚካሄደው       ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ተገቢው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ለድጋፍ ሰልፉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሀዲያ ዞን፣የሆሳዕና ከተማ አስተዳደርና የሌሞ ወረዳ ፖሊስ አባላትና ማኔጅመንት አካላት በመቀናጀት ቀን እና ማታ እየሰሩ እንደሚገኙ አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

በሀዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቭዥን ሃላፊ ኮማንደር ሳህሉ ኃይሌ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ችግሮችን እና አለም አቀፍ ተጽዕኖዎችን ተቋቁሞ የህዝቡ ብርቱ ክንድ የታየበት የድል ብስራት በመሆኑ በድጋፍ ሰልፉ ህዝቡ ያለአንዳች እንቅፋት ደስታውንና ድጋፉን መግለጽ እንዲችል መምሪያው ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

በሌላ በኩልም ከመስከረም 12 እስከ13  የሚከበረው የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ”በዓልና መስከረም 16 የሚከበረው የመስቀል ደመራ ስነስርዓት በሰላም እንዲከበር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝም ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።

በድጋፍ ሰልፉም ሆነ በበዓላቱ ምክንያት በትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮች እንዳይስተዋሉ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር እየተሰራ ስለመሆኑም ተነግረዋል።

ህብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለዞኑ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣም ያሳሰቡት ኃላፊዎቹ የግድቡን መጠናቀቅ በማስመልከትም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ ኤርጡሜ ዳንኤል ከሆሳዕና ጣቢያችን