የከምባታ ዞንን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ተናገሩ

የከምባታ ዞንን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ተናገሩ

”የባህል ልማታችን ለሁለንተናዊ ብልጽግናችን” በሚል መሪ ሃሳብ 10ኛ ዙር የከምባታ ዞን ህዝቦች የባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ልማት ሲምፖዚየም በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ሲምፖዚየሙ በባህል ሽማግሌዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የከምባታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ሀደሮ እንደገለጹት፤ የዘንድሮ በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው።

በዞኑ የብሄረሰቡን ቋንቋ፣ ባህል እና ታሪክ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሼቱ በበኩላቸው፤ በከምባታ ብሔረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የክረምት ወራት ማብቃቱን ተከትሎ በወርሃ መስከረም የሚከበረው የዘመን መለወጫ መሳላ በዓል የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረው የባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ልማት ሲምፖዚየም የሚከበረው በአገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ ድሎች ታጅቦ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና እንደ ዞን 777 የአምበርቾ የቱሪስት መስህብ ተጨማሪ ስራዎች በስኬት መጠናቀቃቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል።

በዞኑ ያሉ ቱባ ባህሎችን ወደ ሀብት ለመቀየር የዞኑ መንግስት ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የከምባታ ህዝብ ከጥንት ይዞ የመጣውን የስራ ባህልን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ በሲምፖዚየሙ ጠንከር ያሉ ውይይቶች እንደሚደረጉም አቶ አረጋ ተናግረዋል።

ባህልን ለማልማት የቋንቋና ታሪክ ልማት ወሳኝ በመሆኑ ቁሳዊና ቁሳዊ ያልሆኑ ባህሎችን መንከባከብና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አክለዋል።

በዞኑ የአምበርቾ 777 የቱሪስት መስህብን ለማልማት በተደረገው ጥረት የዞኑ ተወላጆች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የማንሰራራት ዘመን በትምህርት፣ በጤና በግብርናና በሌሎች መስኮችም ህብረተሰቡን ያሳተፉ በርካታ የልማት ስራዎች መታቀዳቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

በዞኑ አሁን ላይ ያለው አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝቡ በጋራ መስራት አለበት ሲሉም አክለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በእለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዘንድሮው ሲምፖዚየምና የመሳለ በዓል ላለፉት 14 ዓመታት በመላው ኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት በተጠናቀቀበት እና ኢትዮጵያ ዳግም የአድዋን ታሪክ ባበሰረችበት ወቅት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድ ያደረገው ፕሮጀክት እና የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ባህል፣ ቋንቋን እና ታሪክን ለቀጣይ ትዉልድ እያስተዋወቅን መሄድ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አንተነህ፤ ባህሎቻችን ለእድገት ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በተለይ የከምባታ ዞንን የቱሪዝም ማእከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ስለ ልማት ስንመካከር ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በመመካከር አንድነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርበት መሆን አለበት ያሉት አቶ አንተነህ፤ እደሀገር እንደ ክልልና ዞን የማንሰራራት ዘመንን እዉን ለማድረግ የበኩላችንን የምንወጣበት እንዲሆን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከከተማ አስተዳደሮችና ከወረዳዎች እንዲሁም ከሃገር ውጪ የመጡ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በሲምፖዚየሙ ላይም መሣላና አንድነት በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን