“የህብረተሰቡ ተሳትፎ ለተመዘገበው ውጤት ድርሻው የጎላ ነው” – የሲዳማ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ
በካሡ ብርሃኑ
የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የማስፈጸምና አቅም ግንባታ ዘርፍ የበጀት ዓመቱን የስራ አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው ህብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በሀብቱ እያደረገ ያለው ተሳትፎ በከተሞች እየተመዘገበ ላለው የመሰረተ ልማት ግንባታ ድርሻው የጎላ መሆኑን አንስቷል፡፡
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃለፊ እና የማስፈጸምና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ መድሃኒት ከበደ የአመቱን የስራ አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ በከተሞች በመንግስት ካፒታል ፕሮጀክቶች የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በየአመቱ እያደገ የመጣው የህዝብ ተሳትፎ ደግሞ በከተሞች መነቃቃትን እየፈጠረ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
በተቋማቸው መሰረተ ልማትና አካባቢ ልማት፣ የህብረተሰብ ተሳትፎ እና የማዘጋጃ ቤትና የሰው አቅም ግንባታ የተባሉ 3 ዳይሬክቶሬቶች እንዳሉ ገልጸው በእነዚህ ዳይሬክቶሬቶች እንደ ክልል ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም በመገምገም ዕቅድ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ዕቅድን መነሻ በማድረግ በበጀት ዓመቱ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው በዚህም አዲስ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት እና ያሉትንም ሀብቶች ጠግኖ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በከተሞች ላይ እየመጣ ያለው እንቅስቃሴ ከተለመደው የተለየ እየሆነ መምጣቱን የገልጹት ወ/ሮ መድሃኒት፤ ከመንገድ ከፈታና ጠረጋ፣ ከጠጠር መንገድ ግንባታና ከኮብል ስቶን ንጣፍ ባለፈ ሰፋ ያሉ የከተማ መሰረተ ልማቶች እየተስፋፉ የመጡበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ግንባታ የቀድሞ ከተሞችን ገጽታ እየቀየረ ነው ያሉት ኃላፊዋ የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ዶ/ር ኢኒሼቲቭና በአዲስ አበባ የታየውን ተሞክሮ በመውሰድ በሲዳማ ክልል ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ከተሞች በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከተሞች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው፡፡
በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በበጀት አመቱ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ከሆነው በተጨማሪ እየተሰራ ያለው ከ5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማውን ገጽታ ይበልጥ የሚቀይር ነው ብለዋል፡፡ ልማቱ ሲከናወን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባር ስለመከናወኑ ነው የተናገሩት፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራውን በሌሎች ከተማ መስተዳደሮችና የወረዳ ከተሞች ለማስፋት በተሰራው ሥራ የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ተጠናክሮ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም ይርጋዓለም ከተማ ላይ ጠባብ የነበረውን የአስፓልት መንገድ አፍርሰው እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት በከተማው ማህበረሰብ ዘንድ መነቃቃትን እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዳዬ እና ለኩ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመንገድ ማስፋት፣ የእግረኛ መንገድና የአረንጓዴ ልማትን በማካተት የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ወንዶ ገነት ከተማ 2 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ለኮሪደር ልማት የዲዛይን ስራ ተሰርቶ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በከተሞች በራስ አቅም የሚገነባው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ የመቀየር ስራ በክልሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል ያሉት ኃላፊዋ፤ ይህም ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ከነበሩት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለየት ያለ ነው ብለዋል፡፡
ከተሞችን ከገጠሩ ጋር በመሰረተ ልማት ከማስተሳሰር እና ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ከዚህ በፊት አጥሬን አትንኩ የሚለው የከተሞች ነዋሪ ዛሬ ላይ ሀብቱንና ንብረቱን ለዚህ ዓላማ በመስጠት የልማቱ ባለቤት እየሆነ ይገኛል፡፡ ለዚህም በጉልበቱና በገንዘቡ በመሳተፍ አጋርነቱን እያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በክልሉ መንግስት በጀት ታቅደው በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ መንግስት በካፒታል ፕሮጀክት በ2 ከተሞች ላይ ሲከናወኑ የነበሩ የኮብልስቶን ንጣፍ ወደ 4 ከተሞች በማስፋት የተከናወነ ሲሆን በተመሳሳይ የጠጠር መንገድ ግንባታ በ23 ከተሞች 54 ኪሎ ሜትር ማከናወን ተችሏል፡፡ በሶስት ከተሞች ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ቦይ ግንባታ፣ የድልድይ ግንባታ እንዲሁም በሌሎች ሁለት ከተሞች ላይ የድልድይ ግንባታ በመንግስት የካፒታል ፕሮጀክት ታቅደው እየተገነቡ መሆናቸውን ወ/ሮ መድሃኒት ተናግረዋል፡፡
በወንዶ ገነትና ዳዬ ከተሞች የተገነቡ የድልድይ ግንባታዎች የህዝቡን የዘመናት ችግር የፈታና ከጎርፍ አደጋም የታደገ መሆኑን ጠቅሰው ከፍተኛ በጀት በመመደብ 1 ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድም መገንባቱን ገጸዋል፡፡ ወንዶ ገነት ላይም የከተማዋን ገጽታ ሊቀይር የሚችል የድልድይ ግንባታ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም በከተሞች ላይ ለዘመናት በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የሚታደግ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ በለኩ ከተማ 6 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ቦይ እና መልጋ ወረዳ ላይ የሚገነባው ወደ ማለቁ የተቃረበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በበጀት አመቱ በክልሉ በ21 ከተሞች 45 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጠረጋ ስራ ተሰርቶ ጠጠር የማልበስ ደረጃ ላይ ን,ነው ያሉት ወ/ሮ መድሃኒት በየጊዜው የሚከሰተው የግብአት የዋጋ ንረት ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ተግዳሮት ቢሆንም በየጊዜው የዋጋ ክለሳ በማድረግ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ችግሮችን የመቅረፍ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። የጠጠር መንገድም ከዕቅድ ውጪ ጩኮ ወረዳ ላይ 14 ኪሎ ሜትር ተጨማሪ መገንባቱን ጠቅሰው ቦርቻ አንጠጤ እና አለታ ወንዶ ከተሞች ላይ የግንባታ ማሽኖችን በመከራየት ስራዎች እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከኮብል ስቶን ንጣፍ ጋር በተያያዘ ባለፈው አመት በኮንትራክተሮች አቅም ውስንነት ጎርቼ፣ አርቤጎና ያዬ ከተማ ያደሩትን ጨምሮ ቦና እና ይርባ ከተሞች ላይ 2 ኪሎ ሜትር ለመስራት የጫረታ ሂደቱ ተጠናቆ ወደ በግንባታ ሂደቱ መሸጋገሩን አመላክተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 25 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን ንጠፍ ለመስራት ታቅዶ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ ምስራቅ ሲዳማ ዞን፣ ወንዶገነት፣ ይርጋዓለም፣ ዳዬ እና ሌሎች የወረዳ ከተሞች ላይ መገንባት ችለዋል፡፡ የጠጠር መንገድን እና የኮብል ስቶን ንጣፍን ጨምሮ በአመቶ 200 ኪሎ ሜትር ለመገንባት መታቀዱን የገለጹት ኃላፊዋ ከመንግስት ፕሮጀክት ዕቅድ በተጨማሪ ከተሞች በውስጥ ገቢ የሚሰሯቸውን ጨምሮ መቶ በመቶ መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል፡፡
መንገድ ከፈታና ጠረጋን በተመለከተ ከዚህ በፊት ቦታው ተለክቶ የካሳ ግምት ከተሰጠው በኋላ የሚደረገውን የማፍረስ አሰራር በመለወጥ በተሰራው ስራ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል፡፡ በፕላን የሚመሩ ከተሞች ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በበጀት አመቱ አመርቂ ውጤት ስለመመዝገቡ ያነሱት ወ/ሮ መድሃኒት የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት እና ለስራው መሳካት በወሰደው ቁርጠኝነት የተገኘ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህዝቡ በየመንደሩና በየብሎኩ ያሉ የመንገድ ከፈታዎች ላይ እራሱ ተሳታፊና ተባባሪ በመሆን ያሳየው ቁርጠኝነትን በእጅጉ ያደነቁት ኃላፊዋ በዚህም ከ6 እስከ 12 ሜትር ስፋት ያላቸው መንገዶችን የመክፈት ስራ ተሰርቷል፡፡
በዚህም በ2017 በጀት አመት በክልሉ በተለያዩ ከተሞች 217 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ ለማድረግ ታቅዶ 900 ኪሎ ሜትር የከተማ መንገድ መክፈት ተችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ለካሳ ተብሎ የሚከፈለውን በቢሊዮን የሚገመት የመንግስትን ገንዘብ ማዳን ተችሏል ያሉ ሲሆን ይህ አሰራር ለበርካቶችም ተሞክሮ የሆነ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ከመንገድ ከፈታው ጋር ተያይዞ አካባቢዎቹ የውሃና የመብራት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
ከተሞች እንዳያድጉ ፕላን ማነቆ ሆኖ መቆየቱን የገለጹት ወ/ሮ መድሃኒት የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር ተባብሮ በመስራቱ ከተሞች ከታነቁበት አሰራር የታደገ ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ ማሽን በመከራየት ጭምር የከተሞች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከመክፈት ባሻገር ጠጠር የማንጠፍ ስራም የሰሩ ከተሞች አሉ ብለዋል፡፡
ህዝቡ በተገቢው ከተመራ ገንዘቡንና ንብረቱን ለመስጠት የሚሳሳ አለመሆኑ በግልጽ የታየበት አመት ነበር ያሉት ወ/ሮ መድሃኒት ከመንገድ ከፈታ በተጨማሪ ውሃ መስመር ዝርጋታና የመንገድ ዳር መብራት በህዝቡና በማዘጋጃ ቤቶች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ በዚህም 125 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ ለማከናወን ታቅዶ 100 ኪሎ ሜትር በማከናወን የዕቅዱን 80 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
በበጀት አመቱ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ 45 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ለመገንባት ታቅዶ 30 ኪሎ ሜትር ተከናውኗል፡፡ ካልበርት በቁጥር 51 ለማከናወን ታቅዶ 40 ክትርና ካልበርት ተሰርቷል፡፡ ጥልቀትና ስፋት ያላቸው የጎርፍ መውረጃ ቦዮች 8 ኪሎ ሜትር ለመሥራት ታቅዶ ስምንቱንም ማከናወን ተችሏል፡፡ በሁሉም ዞኖች በሚገኙ የወረዳ ከተሞች 37 ኪሎ ሜትር የመብራት መስመር ዝርጋታ ለማከናወን ታቅዶ 100 ኪሎ ሜትር ማከናወን ተችሏል፡፡ የመብራት ማስፋፊያና የትራንስፎርመር ተከላ በማዘጋጃ ቤትና በህዝቡ ትብብር ተከናውኗል፡፡
የተገነቡ የመሰረተ ልማቶች ረጅም እድሜ እንዲሰጡ ከማድረግ አኳያም በመስሪያ ቤታቸው በኩል ጥገና እንደሚሰራ ጠቁመው በአመቱ 3 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመጠገን ታቅዶ 7 ኪሎ ሜትር፣ 5 ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 5 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር፣ 156 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጥገና ታቅዶ 156 ኪሎ ሜትር፣ 4 ነጥብ 6 የዲች ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 7 ኪሎ ሜትር፣ 105 የመብራት ምሶሶዎችን ለመለወጥ ታቅዶ 100 የመብራት ምሶሶዎችን፣ 25 የህዝብ መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 25 ተገንብቶ ለህዝብ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። 3 ቄራ ለመግንባት ታቅዶ 2 ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በበጀት አመቱ በተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ የገለጹት ኃላፊዋ ለ17 ሺህ 790 ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 12 ሺህ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። ይህም በቢሮው በኩል ካፒታል ተበጅቶላቸው ሁሉንም ወረዳዎች ተደራሽ በሚያደርግ መልኩ እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቢሮው ሌላው የሚሰራው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መሆኑን አንስተው በተቀመጠው ስታንደርድ መሰረት አገልግሎትን መስጠት፣ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማዘመን፣ የተገልጋይ እርካታን ደግሞ በጥናት በማረጋገጥ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቅረፍ የቢሮው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በበጀት አመቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ስታንደርድ የወጣላቸው 7 አገልግሎቶች፡- መሬት፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ እሳት አደጋ መከላከል፣ የቄራ አገልግሎት እና የቀብር ቦታ አገልግሎትን እንዳሉ ገልጸው በተቀመጠው ስታንደርድ መሰረት አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ተገልጋዩ ወደ አገልግሎት ሲመጣ በወጣው ስታንደርድ መሰረት አግልግሎቱን በተቀላጠፈ ጊዜ እንዲያገኝ አስቀድሞ መረጃዎችን የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው በመሬት ዘርፍ ብቻ 19 አገልግሎቶች ያሉ ሲሆን ተገልጋዩ በተገለጸው መረጃ መሰረት አሟልቶ ከመጣ በ30 ደቂቃ ብቻ እንደሚስተናገድ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎትን ከንክኪ ነጻ የማድረግና ተገልጋዮች ቤት ሆነው አገልግሎትን የሚያገኙበት አሰራር ለመዘርጋት አሰራርን የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው፡፡ እንደ ሀገር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በአዲስ አበባና አዳማ የተጀመረውን መልካም ተሞክሮ በማስፋት በሀዋሳም የተጀመረ ተግባር እንዳለ ነው ያሳወቁት፡፡ ተገልጋዩ ህዝብ ከፍሎ ለሚያገኘው አገልግሎት ሌላ ክፍያ ሳያስፈልገው አገልግሎት የሚያገኝበት ስራዓትም እየተመቻቸ ነው፡፡ ይህ እንደ ሀገር የተቀመጠና ክልሉም ተቀብሎ እያከናወነው ያለው ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በበጀት አመቱ በ3 ከተሞች ላይ አሰራርን ከንክኪ ነጻ በማድረግ ለመስጠት ታቅዶ በሀዋሳ የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን ይርጋዓለም እና አለታ ወንዶ ላይ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ወንዶ ገነት ሶፍትዌርን በማበልጸግ እየተሰራ ያለ ሲሆን ዳዬ እና ጩኮ ከተሞች ግብአቶችን የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የሁሉም ተግባር ማሰሪያው የተገልጋይን እርካታ ማረጋገጥ ነው ያሉት ወ/ሮ መድሀኒት አገልጋይ ነኝ በሚል ስሜት አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡ አገልግሎቶች በስታንዳርዶች የሚለኩ እና የፈርጅ ተወዳዳሪነታቸውም በዚሁ መሰረት የሚለካ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል በትኩረት ሊሰራው የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ከአገልግሎቶች አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በስታንዳርድ መሰረት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው የተገልጋይ ዳሰሳ ጥናት በማድረግም አሰራርን የማሻሻል ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም በበጀት አመቱ የተገልጋይ እርካታን ከ73 በመቶ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ ሰባቱንም አገልግሎቶች በመለካት የአመቱ አፈጻጸም 73 በመቶ ላይ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ባለፈው አመት እንደ ሀገር በስታንዳርድ መሰረት አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ 3 የክልሉ ከተሞች ተሸላሚ እንደነበሩ አስታውሰው ይርጋዓለም፣ ሀዋሳና አለታ ወንዶ ከተሞች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የቄራ አገልግሎት ከሰው ጤንነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ዘርፍ እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ መድሃኒት ለእርድ የሚቀርቡ እንስሳት ከእርድ በፊት እና ከታረዱም በኋላ ስጋው ይመረመራል፡፡ ሰራተኛው በየሶስት ወሩ የጤና ምርመራ በማድረግ ያለበትን ሁኔታ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ በቄራ ብቻ 40 ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን እነዚህም ተግባራቸውን በአግባቡ ስለመፈጸማቸው ሪፖርት ያቀርባሉ ብለዋል፡፡ ቄራዎች ከማንኛውም እንስሳት ንክኪ ነጻ የማድረግና ንጽህናቸው የተጠበቀ በማድረግ ሂደትም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ሲሉ በዘርፉ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የበጀት አመቱን የህዝብ ተሳትፎን አፈጻጸም አስመልክተው ወ/ሮ መድሃኒት እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በተበታተነ መልኩ ሲሰራ የነበረው የህብረተሰብ ተሳትፎ የተፈጠሩ አደረጃጀቶች በመጠቀም የተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት እንደተገኘበት ነው የተናገሩት፡፡ ህብረተሰቡ ለከተሞች እድገት ህዝቡ ካለው የመልማት ፍላጎት አኳያ ካለካሳ ጥያቄ ንብረቱን ከመስጠት ጀምሮ ቋሚ የሆኑ ሰብሎችን ቆርጦ አንስቷል፡፡ በዚህም በሚኖርበት መንደር ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች እራሱ ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር በመዘርጋት የተፈጠሩ አደረጃጀቶች ሁነኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡
በየአካባቢው ያሉ መልካም ልምዶችን ይበልጥ ለመጠቀም አደረጃጀቶች በየሳምንቱ በመገምገም የማጠናከር ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም በማበረሰቡ ዘንድ ያለውን የልማት አቅም ለመጠቀም አስችሏል ያሉት ኃላፊዋ በበጀት አመቱ ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች ግንባታ 83 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 54 ሚሊዮን 7 ሺህ 135 ብር ከህብረተሰቡ በደረሰኝ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 760 ሺህ ሰው ለማሳተፍ የታቀደ ሲሆን 658 ሺህ 867 ተሳትፏል፡፡ ይህ የህዝብ የጉልበት ተሳትፎ ወደ ገንዘብ ሲቀየር 178 ሚሊዮን 778 ሺህ 631 ለማዳን ታቅዶ 132 ሚሊዮን 331 ሺህ 523 ብር የመንግስትን ወጪ ማዳን ተችሏል፡፡ አያይዘውም ለመሰረተ ልማት ግንባታ ግብዓት ለማሰባሰብ 168 ሚሊዮን 281 ሺህ 552 ብር ታቅዶ 123 ሚሊዮን 342 ሺህ 512 ብር የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
በክልሉ የቡና፣ ጫት፣ ባህርዛፍ፣ እንሰትና ሌሎች የግብርና ስራዎች በስፋት የሚመረቱበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የከፈለው ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ የሆነው ህብረተሰቡ ልማቱ የኔ ነው በማለቱ እና አደረጃጀቶቹ በራሱ ተወያይቶ የወሰነው በመሆኑ በበጀት አመቱ በልማት ስራዎች መነቃቃትን የፈጠረ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
More Stories
“አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል”
የአዲስ ዓመት ተስፋ
“ግድቡም አለቀ ÷ መስከረምም ጠባ…”